ባህላዊና መንፈሳዊ እሴቶች በጥናት የተደገፈ ጥበቃና እንክብካቤ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ባህላዊና መንፈሳዊ እሴቶች በጥናት የተደገፈ ጥበቃና እንክብካቤ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው ገለፁ።
በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት የ2013 ዓ.ም የጉራጌ መስቀል በዓል በተከበረበት ወቅት ነው።
ሚኒስትሯ በዚህ ወቅት በንግግራቸው ባህላዊና መንፈሳዊ እሴቶችን በሰዎች መካከል መቀራረብን፣ መዋደድን፣ መደጋገፍና አንዱ ለአንዱ ማዘንን እንዲማርና ከወላጆች እንዲረከብ እንደ ድልድይ ሆነው የሚያገለግሉ ስለሆኑ በሳይንስ የተደገፈ ጥናት በማድረግ ልዩ ጥበቃና እንክብካቤ ሊደረግላቸው ይገባል ብለዋል።
ይህን ሳይንሳዊ ጥናት በማድረግ ረገድ የመንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ይህን ሃላፊነት ወስደው መስራት ይኖርባቸዋል ሲሉም አሳስበዋል።
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፋሪስ ደሊል በበኩላቸው የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ከሶስቱ የዩኒቨርሲቲ ተልዕኮዎች አንዱ በሆነው የማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ የባህልና ሀገር-በቀል እውቀት ዳይሬክቶሬት አቋቁሞ በቋንቋ፣ በባህል፣ በባህላዊ ዳኝነትና የአስተዳደር ስርዓት፣ በባህላዊ ህክምና እና በኪነ-ጥበብ ጥናትና ምርምሮችን፣ ባህልና ቋንቋን የመጠበቅና የማበልጸግ/የማሳደግ ብሎም የማስተዋወቅ ስራ ለመስራት ጥረት እያደረገ ይገኛል ማለታቸውን ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።