በደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የተመራው ልኡክ በአፋር ክልል በጎርፍ አደጋ ለተጎዱ ዜጎች ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 14 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)በደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው የተመራው ልኡክ በአፋር ክልል በጎርፍ አደጋ ለተጎዱ ዜጎች የ5ሚሊየን ብር ድጋፍ አደረገ፡፡
ልኡኩ በአፋር ክልል በጎርፍ አደጋ የተጎዱ ዜጎችን ለማቋቋም የሚረዳ 2ሚሊየን ብር የሚገመት ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ እና በጥሬ ገንዘብ 3 ሚሊየን ብር ድጋፍ ለአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳደር አስረክቧል፡፡
አቶ ርስቱ ይርዳው ከክልሉ መንግስት የተደረገውን ድጋፍ ባስረከቡበት ወቅት እንደገለጹት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመደጋገፍ የመሻገር ባህላችንን መሰረት አድርገን በጎርፉ ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያደርገውን ጥረት የክልሉ መንግስትም የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል ብለዋል።
በቀጣይም ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀዋል።
የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ በበኩላቸው ÷ የተደረገው ጉብኝትና ድጋፍ በክልሉ ጎርፍ ጉዳት ያደረሰባቸው ወገኖችን ችግር ለማቃለል እንደሚያግዝ ገልፀው ለድጋፉ በተጎጂዎቹ ስም ለክልሉ መንግሰት ምስጋና አቅርበዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው የተመራው ልኡክ በሱልጣን ሀንፍሬ አሊ ሚራ ህልፈተ ህይወት የተሰማዉን ሀዘን በመግለጽ በቦታው በመገኘት ማፅናናታቸውን ከደቡብ ክልል ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡