በ2022 ዓ.ም ሁሉም ዜጎች የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማስቻል እቅድ መያዙን የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 14 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በ2022 ዓ.ም ሁሉም ዜጎች የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማስቻል እቅድ መያዙን የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት አስተማማኝ የሃይል አቅርቦት ያለባትና በመስኖ ልማት የምግብ ዋስትናን እንድታረጋግጥ ለማድረግ እሰራለሁ ብሏል።
ሚኒስቴሩ ይህን ያለው በዘርፉ የ10 ዓመት መሪ የልማት እቅዱ ላይ እያካሄደ ባለው ውይይት ላይ ነው።
በውይይቱ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የስራ ሃላፊዎችና ሰራተኛች እንዲሁም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈጥሮ ሃብት፣ መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።
የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚንስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀል በውይይቱ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት÷ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት አስተማማኝ የሃይል አቅርቦትን በማረጋገጥ ዘርፉ ለሃገሪቱ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ህይወት መሻሻል የበኩሉን እንዲወጣ ይሰራል ብለዋል።
በተለይ አሁን ላይ ያለውን በሃይል ማከፋፈያያና ማሰራጨት ሂደት ውስጥ የሚባክነውን ሃይል ማስቀረት ተገቢ ነው ብለዋል።
ሚንስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ አክለውም በመስኖ ልማት ያለውን እምቅ አቅም በመጠቀም ኢትዮጵያ በውጭ ምንዛሬ የምታስገባቸውን ምርቶች በሃገር ውስጥ ለመተካት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት መስራት እንደሚገባና መሪ የልማት እቅዱ ለዚህ ተገቢ ትኩረት መስጠቱን ነው ያነሱት።
ከዚያም ባለፈ በእቅዱ ላይ በመስኖ ዘርፍ ለተማሩ ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር ትኩረት ተሰጥቷል።
የ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅዱ አሁን ላይ ያለውን የሃይል
ማመንጨት አቅም ከ4413 ሜጋ ዋት በ2022 ዓ.ም ወደ 20 ሺህ ሜጋ ዋት ለማድረስ ታቅዷል።
በተለይም በነፍስ ወከፍ ያለውን የሃይል ፍላጎት ከማሟላት ባለፈ አዳጊ በሆነው ኢኮኖሚ ውስጥ የሚፈለገው የሃይል ፍላጎት ለማሟላት ከውሃ በተጨማሪ የነፋስ እና የጸሃይ ሃይል አማራጮችን በስፋት በመጠቀም ፍላጎቱን ለማሟላት ዕቅድ ተይዟል።
ለዚህም በመንግስት ከሚሰራው ባለፈ በመንግስት እና የግል አጋርነት የተሻለ ስራ ይሰራል ተብሏል።
በሌላ በኩል በገጠርና ከተማ ያለውን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት በእቅዱ ማብቂያ 3 ነጥብ 6 ቢሊየን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ለማድረስ ታቅዷል።
አሁን ላይ በውሃ ሃብቱ ላይ የተደቀኑ እንደ የተፋሰስ መራቆት፣ የውሃ ድንበር አለመከበር፣ የመጤ አረም መስፋፋት እና ሌሎችም ችግሮችን መፍታት ትኩረት ተሰጥቷቸዋል።
በምስክር ስናፍቅ።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።