Fana: At a Speed of Life!

በመሬት መንሸራተት ተዘግቶ የነበረው የአዋሽ ድሬዳዋ መንገድ ዳግም ለተሽከርካሪ ክፍት መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 11 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በመሬት መንሸራተት ምክንያት ተዘግቶ የነበረውከአዋሽ ወደ ድሬዳዋ የሚዘልቀው መንገድ ዳግም ለተሽከርካሪ ክፍት መሆኑ ተገልጿል።

በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የድሬዳዋ ድስትሪክት ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር አንድነት ሰይፉ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮረፖሬት እንደገለፁ፥ ከድሬዳዋ 117 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በቦርዳ እና ካራ ሚሊ መካከል በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት መሬት ተንሸራቶ ከቅዳሜ ምሽት ጀምሮ ዋናው መንገድ ተዘግቶ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ችግሩን ለማስተካከል ትናንት መሞከሩንና በድጋሜ በተስተካከለው መንገድ ከልክ በላይ የጫነ ተሽከርካሪ በመገልበጡ መንገዱ በድጋሜ ተዘግቶ መዋሉን አክለው ገልጸዋል።

ከትናንት ምሽት ጀምሮ በመከላከያ ሰራዊት እና በምስራቅ ሃረርጌ ዞን ትብብር በተሰራው ስራ መንገዱ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉን ተናግረዋል።

በቀጣይም ከመንገዱ መልክአ ምድራዊ አቀማመጥና ከተፈጥሮ የመሬት መንሸራተት ጋር ተዳምሮ መስተጓጎል እንዳያጋጥም ቀጣይ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

ከዚያም ባለፈ መንገዱን በዘላቂነት ለመስራት በፌደራል ደረጃ ከአዋሽ ቁልቢ ድሬዳዋ እና ሀረር ድረስ በአራት ምድብ በሎት ተከፍሎ ጨረታ መውጣቱን ጠቁመው፥ በድሬዳዋ ድስትሪክትም አራት የሚሆኑ ቦታዎች ተለይተው የጥገና ስራ ለመስራት የተለያዩ ማሽነሪዎች እያስመጣን ነው ብለዋል።

በምንይችል አዘዘው

#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.