የግብርና ሚኒስትር አቶ ዑመር ሁሴንን ጨምሮ የፋኦ የኢትዮጵያ ተወካይ በአፋር ክልል የበረሃ አንበጣ ያለበትን ሁኔታ ተመለከቱ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የግብርና ሚኒስትር አቶ ዑመር ሁሴን ፣ ሚኒስትር ዴኤታ ማንደፍሮ ንጉሴን እና የዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) የኢትዮጵያ ተወካዮች በአፋር ክልል የበረሃ አንበጣ ያለበትን ሁኔታ እና እየተከናወኑ የሚገኙ ስራዎችን ተመልክተዋል።
በጉብኝቱ የተሳተፉ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች እና የዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ተወካዮች የበረሃ አንበጣን ለመቆጣጠር እየተከናወነ የሚገኘው ስራ መጠናከር እንዳለበት ገልፀዋል።
ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን የአንበጣ መንጋው በአፋር ክልል 24 ወረዳዎች መከሰቱን በመግለፅ መሬት ያለው ሁኔታ ከባድ መሆኑን በትዊተር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል።
የበረሃ አንበጣውን የመቆጣጠር ስራ ተጠናክሮ እንደቀጠለ የተናገሩት ሚኒስትሩ በስራው ላይ እየተሳተፉ ለሚገኙ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።
የዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ተወካይ ፋጡማ ሰይድ በበኩላቸው የተነገረን እና መሬት ላይ ያለው ነገር ይለያያል ያሉ ሲሆን ችግሩ ከባድ ነው፤ አንበጣውን አላማ አድርገን ካልሰራን ከባድ ተግዳሮት ሊያጋጥመን ይችላል ብለዋል።
ተወካዮ ፋጡማ ሰይድ ከአካባቢው ማህበረሰብ እና ከባለሙያዎች በመወያየት ክፍተቶች እና ተግዳሮቶች መለየታቸውን የገለፁ ሲሆን ችግሩን ለመቅረፍ ከግብርና ሚኒስትር ጋር በመሆን እንደሚሰራ ተናግረዋል።