Fana: At a Speed of Life!

የሱልጣን ሀንፍሬ አሊሚራህ የቀብር ስነ ስርዓት ተፈፀመ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በትናንትናው እለት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የአፋር ሱልጣን ሀንፍሬ ዓሚራህ የቀብር ስነ ስርዓት ዛሬ ተፈፅሟል፡፡
ስርዓተ ቀብራቸው በአሳይታ ከተማ የተፈፀመ ሲሆን በስርዓተ ቀብር ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አደም ፋራህ፣ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ እና የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ሌሎች የፈደራል እና የክልሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ተገኝተዋል፡፡
የጅቡቲ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትም በቀብር ስነ ስርዓቱ ላይ መሳተፋቸው ታውቋል።
የአፋር መንፈሳዊ መሪ የሱልጣን ሃንፍሬ አሊሚራህ አስክሬን ዛሬ ሰመራ ከተማ የገባ ሲሆን፥ አስከሬኑ ሰመራ ከተማ ሲደርስም የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አወል አርባ፣ የኃይማኖች አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች አቀባበል አድርገዋል።
የሱልጣን ሀንፍሬ አሊሚራህ ባደረባቸው ህመም ህክምና ሲከታተሉ ቆይተው በትናንትናው እለት ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ይታወቃል።
የሱልጣን ሀንፍሬ አሊሚራህ በግብፅ እና በአሜሪካ ከፍተኛ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሲሆን፥ በቀዳማዊ ሀይለስላሴ እና በደርግ ዘመነ መንግስት የአፋር ህዝብ ከማእከላዊ መንግስት ጋር ግንኙነት እንዲኖረው ብዙ ስራ ማከናወናቸውን የህይወት ታሪካቸው ያሳያል።
የደርግ መንግስት ከተቃዋሚ ሀይሎች ጋር በ1983 ግንቦት ወር ላይ በለንደን ባደረገው ድርድር ላይ የአፋር ነፃ አውጪ ግንባርን በመወከል ውይይቱ ላይ ተሳታፊ ሆነዋል።
በ1987 ከተደረገው ምርጫ በኋላ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር በመሆን ያገለገሉ ሲሆን፥ ከ2000 ዓ.ም እስከ 2006 ዓ.ም በኩዌት የኢትዮጵያ አምሳዳር ሆነው አገልግለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ውጪ ሆነው የሚታገሉ የፖለቲካ ሀይሎች ወደ ሀገር እንዲገቡ ያደረጉትን ጥሪ ተከትሎ ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸው ይታወሳል።
በ2004 ዓ.ም የአባታቸውን ሱልጣን አሊሚራህ ሀንፈሬ ማረፍን ተከትሎ የአፋር መንፈሳዊና ባህላዊ መሪ ወይም ሱልጣንነትን ተረክበዋል።
በ1942 ዓ.ም በአፋር አሳይታ እንደተወለዱ የሚነገርላቸው ሱልጣን ሀንፈሬ አሊሚራህ የሁለት ወንዶች እና የ5 ሴት ልጆች አባት ነበሩ።
በጥበበስላሴ ጀምበሩ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.