ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በሁለት የአፍርካ ሀገራት የሚያደርጉትን ጉብኝት ጀምረዋል
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በሁለት የአፍርካ ሀገራት የሚያደርጉትን ጉብኝት በዛሬው እለት ጀምረዋል።
ፕሬዚዳንቱ በአይቮሪ ኮስት እና በኒጄር ይፋዊ የስራ ጉብኝት የሚያደርጉ ሲሆን፥ በትናንትናው ምሽትም አይቮሪ ኮስት መግባታቸው ነው የተነገረው።
በአይቮሪ ኮስት ቆይታቸውም በምእራብ አፍሪካ ቀጠና የሚገኙ ጂሃዲስት ሀይሎችን እየተዋጋ ከሚገኘው የፈረንሳይ ጦር ጋር የበዓል ምግብ መመገባቸውም ታውቋል።
በተጨማሪም በአርቮሪኮስት የፈረንሳይ ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ በመገኘትም ከሁሉም የሀገሪቱ ጦር አባላት ጋር ውይይት ማድረጋቸው ነው የተነገረው።
ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በአይቮሪ ኮስት ቆይታቸውም ሽብርተኝነትን መዋጋት ላይ ዓላማ ያደረገ ዓለም አቀፍ አካዳሚ ለማቋቋም ድጋፍ እንደሚያደርጉም ይጠበቃል።
በነገው እለትም ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ወደ ኒጀር ያቀናሉ የተባለ ሲሆን፥ በቆይታቸውም ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ማሃሙዱ ኢሶፉ ጋር ተገናኝተው እንደሚወያዩም ይጠበቃል።
ምንጭ፦ africa.cgtn.com