ለታላቁ ህዳሴ ግድብ በልደታ ክ/ከተማ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከ71 ሚሊየን ብር በላይ ተሰበሰበ
አዲስ አበባ ፣ መስከረም 5 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከአዲስ አበባ ከተማ ልደታ ክፍለ ከተማ በአንድ ወር ብቻ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ከ71 ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰቡ ተገለፀ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ልደታ ክፍለ ከተማ የህዳሴ ግድብ ዋንጫን ለአራዳ ክፍለ ከተማ ያስረከበ ሲሆን÷ በዚህ ወቅት የአዲስ አበባ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡
ይህን አስመልክቶም አቶ ጃንጥራር አባይ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው እንዳሉት በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ በ2012 ዓ.ም በድፕሎማሲው በኩል ስኬት አስመዝግበናል፣ የመጀመሪያውን የውሃ ሙሌትም በድል አጠናቀናል።
ያም ሆኖ በመጪው ሶስት አመታት ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ አሁንም የሁሉንም ርብርብ ይጠይቃል ያሉት አቶ ጃንጥራር ÷የተፈጠረውን ህዝባዊ መነቃቃት አስጠብቀን በ2013 ዓ.ም የግድቡን ወሳኝ ምዕራፍ እንሰራለን ነው ያሉት።
ዛሬ በልደታ ክፍለ ከተማ የታዘብኩትም ይህንኑ ነው ያሉ ሲሆን ÷በክፍለ ከተማው በሁሉም ወረዳዎች የታላቁን ህዳሴ ዋንጫ በማዘዋወር ከሃምሌ 30 /2012 ጀምሮ ከ71 ሚሊየን ብር በላይ ተሰብስቧል ብለዋል።
ለዚህም መላው የክፍለ ከተማ ነዋሪዎችን ፣ አመራሮችን እና ባለ ሀብቶችን አመስግነዋል።
ዋንጫውንም ተረኛ የሆነው አራዳ ክፍለ ከተማ ተረክቧል፡፡
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።