ኦነግ እንዲያገግም፣እንዲጠነክር፣አሳታፊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ለማድረግ የተጀመረው ትግል ይቀጥላል አለ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኦሮሞ ነጻነት ግንባር እንዲያገግም፣እንዲጠነክር፣አሳታፊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ለማድረግ የተጀመረው ትግል ይቀጥላል አለ።
ሙሉውን መግለጫ ከታች ያንብቡ
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር እንዲያገግም፣ እንዲጠነክር፣ አሳታፊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ለማድረግ የተጀመረው ትግል ይቀጥላል።
(ከኦሮሞነጻነትግንባርየተሰጠሰፊ መግለጫ)
ኣንድን የፖለቲካ ድርጅት ትክክለኛና ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ሊያደርገው የሚችለው የሚገዛበት ዴሞክራሲያዊ ህገ ደንብ፣ የጠራ የፖለቲካ ፕሮግራም፣ ግልጽ ስትራቴጂና የትግል ስልት፣ የሚመራበት የስነ ምግባር ደንብ ሲኖረውና እነዚህንም ተግባራዊ ሲያደርግ ብቻ ነው። የኦሮሞ ነጻነት ግንባር መስራች ጉባዔ ሰኔ 1968 ተቀምጦ የግንባሩ የፖለቲካ ፕሮግራምና ህገ ደንብ ላይ ተወያይቶ በማጽደቅ የተሟላ ድርጅታዊ መዋቅር ዘርግቶ እንቅስቃሴ ከጀመረ እነሆ 44 ዓመታት ኣልፎታል።
ይሁን እንጂ በተለያዩ ጊዜያት ለሚጣሱ የስነ ስርዓት ህጎች አግባብ ያለው መፍትሄ ከመስጠት በእልህና በማን ኣለብኝነት በድርጅቱ ውስጥ በሚነዙ አፍራሽ ፕሮፓጋንዳዎች መከፋፈሎች እንደነበሩ ይታወቃል። በተለይም ከ1991 ዓም ጀምሮ በድርጅቱ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት ታይቶ አይታወቅም። በተለይም ደግሞ ከ1992 ዓም ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ በኦነግ ሊ/መንበር በአቶ ዳውድ ኢብሳ አመራር ስር ድርጅቱ ሶስት ትላልቅ የመከፋፈል አደጋዎች ኣጋጥመውታል።
በአቶ ዳውድ አመራር ስር ድርጅቱ የተለያዩ ውድቀቶች ገጥመውታል። ባጠቃላይ ድርጅቱ የሚጠበቅበትን ተልዕኮ መወጣት ለምን አልቻለም የሚለው በብዙዎች ለዓመታት ሲጠየቅ ለነበረው ጥያቄ ተገቢ መልስ መስጠት ያስፈልጋል።
የታሪክ ኣጋጣሚ ሆኖ አቶ ዳውድ ኢብሳ ወደ ኦነግ ሊ/መንበርነት የመጡት በፈረንጆቹ 1999 ወይም እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1991 ዓ ም ነበር።
ይህም በድርጅቱ ጠቅላላ ጉቦዔ ሳይሆን በ1991 አነስተኛ ቁጥር የነበረውና በአስቸኳይ በተቀመጠ የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ነበር። በዚያን ጊዜ የተቀመጠው የኦነግ ማዕከላዊ ኮሚቴ ከወሰናቸው ውሳኔዎች መካከል ኣንዱ ስድስት ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባዔ ተደርጎ አዲስ መሪ እንድመረጥ የሚል ሲሆን አቶ ዳውድ ኢብሳን በሊ/መንበርነት የመረጠው በጊዜያዊነት ነበር።
ይሁን እንጂ አቶ ዳዉድ ኢብሳ ወደዚህ ሃላፍነት ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ ድርጅቱንና የኦሮሞን ህዝብ ትግል ወደፊት ከማራመድ ይልቅ ራሳቸውን የሁሉም ነገር ማዕከል ኣድርገው ስልጣናቸውን ለማጠከር ከመስራት ውጭ ለኦሮሞ ህዝብ ትግል ያበረከቱት አስተዋጽዖ በጣም ጥቂት ነው። ስድስት ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ እንዲካሄድ ተወስኖ የነበረው የድርጅቱ 3ኛ ጠቅላላ ጉባዔም ተጓቶ ለአምስት ዓመት እንድራዘም ተደረገ።
ከጠቅላላ ጉባዔው መጓተትና ከሚደርስባቸው የተላያዩ ጫናዎች ጋር በተያያዘ እንዲሁም የድርጅቱ ህገ ደንብና አሰራር ተፋልሷል፣ አባላት መብታቸውን ተነፍገዋል በማለት ጥያቄ ያነሱ ብዙ ልምድ ያካበቱ የድርጅቱ አመራሮችና አባላት በ1993 ዓ ም ድርጅቱን ለቀው እንዲወጡ ተደረገ። በዚህ ምክንያት ከድርጅቱ የወጡ ነባር የአመራር አባላት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የሽግግር አመራር በሚል ስያሜ ራሳቸውን ሲያደራጁ ግንባሩ ለሁለት ተከፈለ።
አሁንም ከግንባሩ 3ኛ ጠቅላላ ጉባዔ በኋላ በ2000 ዓም ለሁለተኛ ጊዜ በአቶ ዳዉድ ስር ኦነግ ለሁለት ተከፍሎ በርካታ የበሰሉና ልምድ ያላቸው የአመራር አባላት ከድርጅቱ ወጥተው የኦነግ ጊዚያዊ ኮሚቴ በሚል ተደራጁ።
በወቅቱ የተፈጠሩ አለመግባባቶችን በአግባቡ ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶች በሊ/መንበሩ ገታራ አቋምና አካሄድ ሳይሳኩ ቀርተው ግንባሩ ለሁለት ተከፈለ። አቶ ዳዉድ በ2000 ዓ ም መካሄድ የነበረበት ጠቅላላ ጉባዔ ተካሂዶ አዲስ መሪ እንዳይመረጥ ሆነ ብለው በማስተጓጎል ድርጅቱ ለሁለት ተከፍሎ በአንደኛው ኣንጃ ሊ/መንበር ሆነው መቀጠልን መረጡ።
በድርጅቱ ውስጥ ችግር እንድፈጠር ያደረጉበት ምክንያትም የስልጣን ዕድሜያቸውን ለማራዘም በማሰብ ነው። እሳቸው የማይመሩት ኦነግ እንዳይኖር ለማድረግ ሌት ተቀን የሚሰሩ መሆናቸውን በተላያዩ አጋጣሚዎች የተረጋገጠ ጉዳይ ነው።
ይህ ብቻ ሳይሆን እንደገና በኢትዮጵያ አቆጣጠር 2003 ዓም ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር በተለያዩ ጊዜያት ወጥተው ኣንጃ ከፈጠሩ ድርጅቶች ጋር ድርድር ተደርጎ ግንባሩ ወደ ቀድሞ ኣንድነቱ እንዲመለስ በነባር አባላትና የድርጅቱ መስራቾች የተደረገው ጥረት በማጨናገፍ እንዳይሳካ ያደረጉት አቶ ዳውድ ኢብሳ ነበሩ።
በዚህ ምክንያት የኦነግን ድርጅታዊ ኣንድነት የደገፉ የአመራርና በርካታ የግንባሩ አባላት “የውስጥ ጠላት” ተብለው ተፈርጀው ድርጅቱን ለቀው እንዲወጡ ተደረገ።
በ2003 ግንባሩን ለቀው የወጡ የድርጅቱ አመራርና ነባር አባላት ተሰባስበው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር የሚል ድርጅት ሲያቋቁሙ ግንባሩ አሁንም ለሶስተኛ ጊዜ በአቶ ዳዉድ አመራር ስር ተከፈለ። ቀደም ስል በተፈጠሩ መከፋፈሎችና በኋላ ላይ በ2003 ዓ ም በተፈጠረው መከፋፈል በድርጅቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል።
በ2000 ዓ ም መካሄድ የነበረበት ጠቅላላ ጉባዔም እስከ 2009 እንዲቆይ ተደርጎ አቶ ዳውድ ኢብሳ ከድርጅቱ ህገ ደንብ ውጭ ስልጣናቸን ለዘጠኝ ዓመት ኣራዘሙ።
ከ13 ዓመት በኋላ በ2009 ዓም አሁንም ኤርትራ ውስጥ በተቀመጠው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ኣቶ ዳውድ ኢብሳ ታማኝ የሆኑ የራሳቸውን ሰዎች በአስመራጭነት ሰይመው ከ18 የስልጣን ዓመታት በኋላ እንደገና እንድመረጡ ተደረገ። እነሆ የድርጅቱ ሊ/መንበር ሆነው የስልጣን ወንበሩን ከተቆናጠጡ 21 ዓመት ኣስቆጥረዋል።
አመራር ራሱን የቻለ ጥበብ ኣለው። የአንድ መሪ ችሎታ የሚለካው በአመራር ዘመኑ በሚያስመዘግበው ውጤት ነው። ኣንድ መሪ ለሌላ ሰው ምሳሌ መሆን፣ ኣርቆ ኣስተዋይ፣ እውነት ላይ ተመስርቶ በሀቀኝነት ሲሰራና ተዓማኒነት ያለው ሰው ሆኖ ከራሱ ጥቅም የህዝብን ጥቅም የሚያስቀድም ፣ችሎታና ራዕይ ያለው ሲሆን ነው።
ኣንድ መሪ ብዛትና ጥራት ያላቸውን ተከታዮች ማፍራት ይጠበቅበታል። ጠንካራ መሪ አስመሳዮችን ሳይሆን ነገ ተተኪ መሪዎች መሆን የሚችሉ ብቃት ያላቸውን እያፈራና እየቀርጸ መሄድ የሚችል መሆን ኣለበት። አቶ ዳውድ ኢብሳ ፈጽሞ የዚህ ሰው መሆን አልቻሉም። ችሎታውም ፍላጎቱም የላቸውም።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ድርጅታዊ መርህ የአንድ ግለሰብ አመራር ሳይሆን የጋራ አመራር (Collective leadership) ላይ የተመሰረተ መሆኑ በድርጅቱ ህገ ደንብ ወስጥ ተድንግጓል። ማንም ይሁን ማን ግለሰብ ለድርጅቱ ይታዘዛል፣ ኣናሳ ድምጽ ለብዙኋን ድምጽ ይገዛል፣ በብዙሃን የተወሰነ ውሳኔ በሁሉም ዘንድ ተግባራዊ ይሆናል፣ የህግ የበላይነት መከበር የግድ ነው።
አቶ ዳዉድ ኢብሳ የጋራ አመራር ከመስጠት ይልቅ የራሳቸውን ፍላጎትና የስልጣን ጥማት ለማርካት ሲባል ለ 21 ዓመታት የኦሮሞ ነጻነት ግንባርን ኣቀጨጩት።
በሃሳብና በሪዮተዓለም ሳይሆን የሀሰት ፕሮፓጋንዳና ውዥንብር በድርጅቱ ውስጥ በመንዛትና በማስነዛት ነበር የኖሩት። ዛሬም ይህንኑ እያራመዱ እንደሚገኙ የአደባባይ ሚስጥር ነው። ርካሽ ፕሮፓጋንዳና በሀሰት ወሬዎች ብልሹ አሰራሩንና ኣካሄዱን የሚተቹ አመራሮችና ኣባላት ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻን ማካሄድ ቋሚ ስራቸው ኣድርገዋል። በዚህ ድርጊታቸው የኣባላት ብዛት እና ጥራት በእጅጉ እንዲቀነስ በማድረግ የኦሮሞ ነጻነት ግንባርና ትግሉን ኣመነመኑት።
ለድርጅቱ መዳከም ቀደም ስል የነበሩ ሌሎች የድርጅቱ ከፍተኛ አመራርም በቸልተኝነት በማለፋቸው ተጠያቂዎች ቢሆኑም አቶ ዳውድ ኢብሳ ለድርጅቱ መዳከም ዋና ተጠያቂ ናቸው። ለራቸው ፍላጎትና ጥቅም ሲሉ የኦሮሞ ነጻነት ግንባርን ትግል ክፉኛ ጎድተውታል ብለን እናምናለን። ራሳቸውን እንደ መሪ ሳይሆን እንደ ንጉስ የሚቆጥሩ፣ በዙሪያቸው የተኮለኮሉ የመንደር ሰዎችን እንጂ ሌላውን የማይሰሙ ናቸው።
ዘመዶቻቸውና የመንደራቸው፣ እንዲሁም በጥቃቅን ጥቅማ ጥቅሞች የሚደለሉ ግለሰቦችም እሳቸውን ለማንገስና ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ በድርጅቱ ውስጥ ለውጥ ኣንዳይመጣ እንቅፋት ሲሆኑ ኖረዋል።
አቶ ዳዉድ ኢብሳ በሊ/መንበርነት በቆዩባቸው 21 ዓመታት የድርጅቱን ገንዘብና ሀብት ብቻቸውን ሲያዙበት ኖረዋል። በድርጅቱ ውስጥ አድልዎ በመፍጠር የአከባቢያቸውን ሰዎችና ዘመዶች ቁልፍ የስራ መደቦች ላይ በመመደብ ጥቅማቸውን አስጠብቀዋል። በዚህ መሰል ኣካሄድ ከድርጅቱ ህገ ደንብና አሰራር ውጭ የራሳቸውን አምባገነንነት በድርጅቱ ላይ ኣንግሰዋል። አቶ ዳዉድ ኢብሳ 21 ዓመት በሊ/መንበርነት በቆዩበት ጊዜያት ድርጅቱ ፈራርሶ ከነበረበት ወረደ እንጂ እድገት አላሳየም።
በአመራር ዘመናቸው የኦነግ ኮር አመራርና መዋቅሩ እንዲፈርስ ተደርጓል። የጋራ አመራር የሚለዉ በሃሳብ እንጂ በተግባር ሊታይ አልቻለም።. በአቶ በዳዉድ ኢብሳ አመራር ያልረኩ እዉቀትና ቸሎታ ያላቸዉ በርካታ አባላት በየጊዜዉ ድርጅቱን ለቀዉ ወጥተዋል። ዛሬ ኦነግ ዉስጥ የተማሩና ልምድ የቀሰሙ አባላት ቁጠር አነስተኛ ነዉ፡፡
ድርጅታዊ መዋቅር ጠብቆ ከመስራት፡ በመዋቅር ዉስጥ መዋቅር በድርጅት ዉስጥ ስውር ደረጅት ዘርግቶ በመቆላለፍ በአባላት መካከል ጥርጣሬና መከፋፈል እንድኖር ማድረግ የተለመደ ሆኗል፡፡ ዛሬም ይህ በገሃድ የሚታይ ነው።
በአገር ዉስጥ የሚካሄደዉን የድርጅቱን ስራ ሌሎች የድርጅቱ አመራሮች እንዳያዉቁትና እንዳይሳተፉበት በማደረግ ከመንደራቸው ጥቂት ሰዎች ጋር ሆነው በመቆጣጠር እንዳሻቸዉ ሲያደርጉ ቆይ ተዋል፡፡ አገር ውስጥ የነበረዉ መዋቅር በብዛት በወያኔ የደህንነት መዋቅር እጅ ነበር ማለት ይቻላል፡፡
ሊ/መንበሩ ያደራጁዋቸው በወያኔ መዋቅር ዉስጥ የሚሰሩ የአከባቢያቸዉ ሰዎች ነበሩ፡፡ ለዚህም ግርማ ጥሩነህ የሚባለዉ ዘመዳቸው አይነተኛ ምሳሌ ነዉ፡፡ ግርማ ጥሩነህ በርካታ የኦሮሞ ወጣቶቸና ታጋዮችን ሲያሳስር የነበረ የወያኔ ሰላይ ነበር፡፡ የግርማ ጥሩነህን ጉዳይ እንዲያጣራ በድርጅቱ የተሰየመው ኮሚቴ ግለሰቡ ከወያኔ ጋር የሚሰራ መሆኑነ ቢያረጋግጥም በኣቶ ዳዉድ ኢበሳ ተቀባይነት አላገኘም፡፡
ይባስ ብለው ከድርጅቱ አመራር ተዉጣጥቶ ጥናቱን ያካሄደዉን ኮሚቴ በመወንጀል አንዲገለሉ ተደርጓል።
በትጥቅ ትግሉም በኩል በቂ ጥናትና ዝግጅት ሳይደረግበትና ከሌሎች የድርጅቱ አመራሮች ጋር ሳይመከርበት በተለያዩ ጊዜያት አቶ ዳዉድ ኢብሳ ያሰማሯቸዉ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አመርቂ ዉጤት ሳያስገኙ በወያኔ ሠራዊት እጅ ገብተው ጉዳት ስደርስበት ቆይቷል። ሆኖም ላደረሱት ኪሳራዎችና ዉድቀት ኣንድም ጊዜ ተጠያቂ ሆነው አያዉቁም፡፡ ባጠቃላይ አቶ ዳዉደ ኢብሳ ገና ወደ ሊ/መንበርነት በመጡ ማግሰት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ዋና መቀመጫ ወደ አስመራ፣ ኤርትራ መዛወሩ በሳቸው ለሚሰራዉ ጥፋት ተጠያቂ ለማድረግ አልተቻለም።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ከ27 ኣመት በኋላ ሰላማዊ የትግል ስትራቴጂን መርጦና ወስኖ ከኢትጵያ መንግስት ጋር ተደራድሮ 2010 ኣ.ም ወደ አገር ቤት መመለሱ ይታወሳል፡፡ ወደ አገር ቤት ሲመለስ ያኔ ኦሮሚያን ሲያስተዳድር የነበረዉ ኦህዲድን ጨምሮ ከሌሎች የኦሮሞ ድርጅቶች ጋር የኦሮሚያንና የኦሮሞን ህዝብ ጥቅም ለማስከበር አብሮ ለመስራት መወሰኑም ይታወሳል።
አቋሙንና ፖሊሲዎቹንም በሄደበት ሁሉ ለህዝቡ ኣሳውቋል። የኦሮሞ ህዝብም ኦነግ ወደ አገር ቤት መመለሱን ከሁሉም አከባቢዎች በሚሊዮኖች ወጥቶ የተቀበለዉም ሰላማዊ ትግሉን በመደገፍ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ እንኳን በደህና ወደ ሰላማዊ ትግል መጣችሁ በማለት ተቀበለን እንጂ የትጥቅ ትግሉን ትታችሁ ለምን መጣችሁ አላለንም፡፡
ይሁን እንጂ ኤርትራ ማስልጠኛ ካምፕ ዉስጥ የነበሩ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አባላት በሰላማዊ መንገድ ወደ አገር ቤት ቢገቡም የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ዋና አዛጅ የሆኑት አቶ ዳዉድ ኢብሳ አገር ውስጥ የነበሩ የሰራዊቱ አባላት ወደ ሰላማዊ ትግል እንዲመለሱ ለማድረግ የሚጠበቅባቸውን አላደረጉም፡፡
በመንግሰት በኩልም የነበረዉ ችግር እንዳለ ሆኖ አቶ ዳዉድ ኢብሳ “ማን ማንን ያስፈታል” በማለት በሚዲያ ያስተላለፉት መልዕክት ጥርጣሬን በማንገስ ለመንግሰት ወታደራዊ እርምጃ በር ከፍቷል፡፡ የትግል ስልት ጥበብን ይጠይቃል። አቶ ዳዉደ ኢብሳ አዲስ አበባ ከተማ ተቀምጠው የትጥቅ ትግልን ለመምራት የሚያደርጉት አጉል ጥረት ድርጅቱ በሰላማዊ መንገድ በሚያደርገዉ ትግል ላይ ትልቅ ተጽእኖ መፍጠሩ ኣለ የማይባል ሀቅ ነዉ፡፡
ከተቀሩት የድርጅቱ አመራር አባላት በመደበቅ የሚፈጽሟቸው ህገ ወጥ ድርጊቶች በድርጅቱ አመራር ዉስጥ የሰፋ ልዩነት እንድፈጠር ምክንያት ከሆኑት መካከልም ይሄኛዉ ዋናዉና ትልቁ መሆኑን ለህዝባችንና ለወዳጆቻችን መግለጽ እንወዳለን፡፡
ሰላማዊ ትግልንና የትጥቅ ትግልን ቀላቅሎ ማካሄድ ድርጅቱን መጉዳቱ በግልጽ ታይቷል።፡ አቶ ዳዉድ ኢብሳ በወቅቱ በኦነግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተላለፈዉን ውሳኔ ወደ ጎን በመተዉ በትጥቅ ትግል የተሰማሩ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አባላትን ለአባ ገዳዎችና ለኦሮሞ ህዝብ ሰጥቼሃለሁ ማለታቸውም የጋራ አመራርን ውሳኔ ያፋለሰ እና ሌላኛዉ የስልት ስህተት መሆኑንም በዚሁ አጋጣሚ ጠቀሰን ማለፍ እንወዳለን፡፡
ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴዉ ይህንን አባባል በዝምታ የተመለከተዉ የድርጅቱን ኣንድነት ለመጠበቅ እንጂ ኣምኖበት እንዳልነበረ በዚሁ አጋጣሚ መግለጽ እንፈልጋለን፡፡
ይህ በአንዲህ እንዳለ ከኦነግ ከፍተኛ አመራር ውስጥ ሊ/መንበሩ ያሰማራቸው ጥቂት ግለሰቦች የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊትን መቀላቀላቸውና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሰራዊት ከፍተኛ አመራር በማለት በትጥቅ ትግል መቀጠል መምረጣቸውን ማወጃቸው፣ አንዲሁም ጥቂት አባላት በቴሌፎን ሰራዊቱን ለመገናኘት መሞከርና የሰላማዊ ትግሉን ስነ ምግባር ያለማክበር ድርጅቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።
በተለይም በወለጋና ጉጂ የሚኖረው ህዝባችን ላይ ከፍተኛ ወከባ፣ የአገር ውስጥ ስደት፣ የህይወትና የንብረት ጉዳት በማስከተል የህዝቡን የመንቀሳቀስ ነጻነትና ሰላማዊ ኑሮ ኣናግቷል።
በውጭ ያሉ ጥቂት የድርጅቱ አመራር አባላት የነበሩ ግለሰቦችም ከትጥቅ ትግል ውጪ የሚያዋጣን የለም በማለት ገንዘብ በማሰባሰብና በየጊዜው በማህበራዊ ሚዲያና በONN ቴሌቪዥን ላይ ወጥተው በኦነግ ስም የሚያስተላልፉት መልዕክትና የሚያደርጉት ቅስቀሳዎችና ጥሪዎች ከድርጅቱ የትግል ስትራቴጂና ከሀገሪቷ ህግ ጋር የሚጣረዙ በመሆናቸው በድርጅቱ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል።
ከፊል የድርጅቱን የአመራር አባላት የትጥቅ ትግል ደጋፊዎች፣ ሌሎችን ደግሞ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል የሚፈልጉና ከመንግስት ጋር ያበሩ በማለት የስም ማጥፋት ዘመቻ እያካሄዱ ራሳቸውን ወደር የማይገኝለት የነጻነት ታጋይ አስመስለው በማቅረብ በድርጅቱ ውስጥ መከፋፈል አንዲኖር በሰፊው ዘመቻ አካሂደዋል።
ይህም በአመራሩ ውስጥ ክፍፍል ፈጥሮ የድርጅቱን በሰላማዊ መንገድ የመታገል ውሳኔ አክብረው ለተግባራዊነቱ የሚሰሩትን ስም ለማጥፋት ግልጽና ሰውር ቅስቀሳ ማካሄድ ዕለታዊ ተግባራቸው ሆኗል። ከድርጅቱ ደንብና ስነ ስርዓት ውጭ የተለያዩ ሰዎች በተለያዩ ስሞች በፌስ ቡክና በሚዲያ ወጥተው አብዛኛውን የአመራር አባላት የተለያዩ ስሞችን በመስጠት በሚያካሄዱት የስም ማጥፋት ዘመቻዎች የድርጅቱን አባላትና ደጋፊዎችን ውዥንብር ውስጥ አንዲገቡ ለማድረግ ሞክረዋል።
ኦነግ ወደ ሃገር ቤት ከተመለሰ በኋላ ድርጅቱ ከህዝብ ጋር ለመገናኘት ያገኘውን ዕድል በመጠቀም የድርጅቱን አመራርና መዋቅር ማሻሻልና ማደስ አለብን ብለው አብዛኛው የአመራር አባላት ሃሳብ ቢያቀርቡም በአቶ ዳውድ ኢብሳ ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም።
የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደር እስካሁን ሁነኛ ጠቅላላ ጉባዔ ሊደረግ አልቻለም። ግልጽና ነጻ ምርጫ ተካሂዶ ሀገር ውስጥ ከነበሩ አባላት ውስጥ ብቃት ያላቸው ሰዎች ወደ አመራርነት እንድመጡ ሃሳብ ቢቀርብም ይህንን ጥያቄ ወደጎን በመተው ነባር አመራሩ ብቻ በአመራር እንዲቀጥል ተወሰነ። ዛሬም ቢሆን አቶ ዳዉድ ኢብሳ በታህሳስ 2013 ሊደረግ የተወሰነውን ጠቅላላ ጉባዔ ለማደናቀፍ አስቀድመው ድርጅቱ ውስጥ ችግር በመፍጠር ከድርጅቱ ደንብና ስነ ስርዓት ውጪ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ።
ጠቅላላ ጉብዔ የሚያስፈልገው ድርጅቱ የሚከተለውን ስትራተጂና ታክቲክ፥ አመራርን ለማደስ፣ በፖለቲካ ፕሮግራሙና በድርጅቱ የመተዳደሪያ ደንብ ላይ ሰፊ ውይይት በማካሄድ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ኣጣጥሞ ትግሉን ወደፊት አንዲራመድ ለማስቻል ነው። አንድ የፖለቲካ ድርጅት ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ለመራመድ የሚያስችለው ተሃድሶ ካላካሄደና ታክቲክና ስትራተጂውን በመገምገም የእርምት እርምጃዎችን አየወሰደ ካልተራመደ በሂደት መክሰሙ የማይቀር ነው።
የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በተመለከተ ሁሉም ማለት በሚቻል ደረጃ ከኦነግ የወጡ ናቸው ማለት ይቻላል። በመሆኑም በመካከላቸው ጉልህ የሆነ ልዩነት አንደሌለ ይታወቃል። በመሆኑም በተፈጠረው መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ያሉትን ጥቃቅን ልዩነቶች በማሰውገድ በአንድ ጥላ ስር በመሰባሰብ የትግሉን ጎራ ማጠናከር የሚል የኦነግ ቋሚ ፖሊሲና ጽኑ አቋም ነበር። የህዝባችን ጥያቄም የኦሮሞ ፖለቲካ ድርጅቶች አንድነት ፍጠሩ የሚል ነው። ይህን ጥያቄ ለመመለስ ሙከራዎች ቢደረጉም አቶ ዳዉድ ኢብሳና የተወሰኑ የአመራር ኣባላት ፍላጎት በማጣት ለብቻ መታገልን በመምረጣቸው ሊሳካ አልቻለም።
ይህን በሚመለከት የኦነግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የጋራ አመራር ውሳኔን ለማክሸፍ በሃሰት የስም ማጥፋትና ርካሽ ፕሮፓጋንዳዎችን በመጠቀም የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ህብረትና አንድነት እውን አንዳይሆን ተደርጓል። በዚህም ምክንያት የኦሮሞ ነጻነት ትግል ጎራ አንዳይጠናከርና አንዳይረጋጋ ሆኗል።
ዛሬ በአመራሩ ድክመት ኦነግ ቀደም ስል የነበረው ክብር፡ ድጋፍና ተቀባይነት ተሸርሽሮ እየተመናመነ መሆኑ ግልጽ ነው። ህዝቡ የነጻነት ትግሉን በእጁ ኣስገብቶ ያለ በቂ አመራር በራሱ መንገድ ታግሎ መስዋዕትነትን ከፍሏል። እየታገለም ነው። የኦሮሞ ህዝብ በድርጅቱ ዓላማ፣ ስምና ዓርማ ስር ተሰልፎ ታገለ አንጂ የአንድን ግለሰብ የበላይነት ከተጸየፈ ሰነባብቷል። ስለሆነም የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ከላይ የተገለጹትን ግምገማዎችን ካካሄደ በኋላ የሚከተሉትን ውሳኔዎችና አቋሞችን ወስዷል።
1. አቶ ዳዉድ ኢብሳ ላለፉት 21 ዓመታት በላይ በአመራር ላይ በቆዩበት ግዜያት በድርጅቱ ላይ ባደረሱት ጉዳትና መበታተን በተጨማሪ ባሁኑ ወቅትም ከድርጅቱ ህግና ስርዓት ውጪ የሃሰት ፕሮፓጋንዳና የስም ማጥፋት ዘመቻን በድርጅቱ አመራሮች ላይ በማካሄድ በድርጅቱ ውስጥ ውዥንብርና መደናገር አንዲፈጠር አድርገው ድርጅቱን ለ4ኛ ግዜ በመክፈል ላይ ይገኛሉ።
በመሆኑም ጉዳያቸው ተጣርቶ በቀጣዩ የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ውሳኔ አስኪያገኝ ድረስ የሰራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ነሓሴ 1, 2012 በወሰነው መሰረት አሁንም ከድርጅቱ ሊ/መንበርነት ታግደው እንደሚቆዩ ለድርጅቱ አባላት፣ ለደጋፊዎቹ፣ ለኦሮሞ ህዝብና ለሌሎች አካላት በድጋሚ እናሳውቃለን። አቶ ዳዉድ ኢብሳ ከድርጅቱ ደንብና ስርዓት ውጭ የድርጅቱን ሀብትና ንብረት በመቆጣጠር ለፈለጉት ብቻ ከማዋላቸው በተጨማሪ ከድርጅቱ ህግና ስርዓት ወጭ የግል መዋቅር በመዘርጋት ላይ አንዳሉ አያሳወቅን ህዝባችን ኦነግን ለ 4ኛ ጊዜ ለመናድ አየተሸረበ ያለውን የሴራ ፖለቲካና አፍራሽ ድርጊት ከጎናችን ቆሞ አንዲታገለው ጥሪያችንን እናስተላልፋለን። እኛም አጥብቀን የምንታገል መሆናችንን እናረጋግጣለን።
2. የድርጅቱ ንብረትና ሃብት የጋራ ወይም የአባላት በሞላ አንጂ የግል አይደለም። የድርጅቱ አባላት ሀብት ንብረታቸውን የማወቅም ሆነ የመቆጣጠር መብት አላቸው። ይሁን አንጂ ላለፉት ሁለት አመታት የድርጅቱ የገቢ ምንጭ ከየት አንደሆነ፡ ለምንና አንዴት አንደሚወጣ አንኳን ኣባላት ለድርጅቱ አመራር ሪፖርት ቀርቦ አያውቅም። የፋይናንስ ስርዓት ተዘርግቶ በስርዓት ተግባር ላይ አየዋለ አንዳልሆነ በግልጽ የሚታይ ነው።
በድርጅቱ ስምና በግል በተከፈቱ የባንክ አካውንቶች ውስጥ ገብቶ የነበረው ገንዘብም እየተዘረፈ ለግል ጥቅም ኣየዋለ መሆኑን አባሎቻችን እንዲያውቁት እንፈልጋለን። ይህ ጉዳይ በሚመለከተው አካል ተጣርቶ ለህግ በማቅረብ አስፈላጊውን ውሳኔ እንደሚያገኝ ለአባሎቻችንና ለህዝባችን በዚሁ አጋጣሚ መግለጽ እንሻለን።
3. ኦነግ ለጋራ አመራር አንጂ ለግለሰብ አመራር ቦታ የለውም። የኦነግ መተዳደሪያ ደንብም ይህንኑ ያረጋግጣል። ይሁን አንጂ አቶ ዳዉድ ኢብሳ የድርጅቱ ህገ ደንብ ያልሰጣቸውን ስልጣን ያላቸው በማስመሰል በግል የወሰዱትና አየወሰዱ ያሉት ህገ ወጥ አርምጃዎች በምንም ሁኔታ ተቀባይነት አይኖረውም።
የኦነግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በአቶ ዳዉድ ኢብሳ እየተወሰዱ ያሉትን ህገ ወጥ አርምጃዎች አያወገዘ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ከሳቸው ጋር በመወገን አፍራሽ ተልዕኮ ላይ የተሰማሩ ኣንዳንድ አባላት ወደ ትክክለኛው የትግል መስመር አንዲመለሱ እንመክራለን።
4. የኦነግ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ድርጅቱ በሰላማዌ መንገድ ለመታገል ወስኖ ወደ አገር ቤት የተመለሰበትን የትገል ስትራቴጂ አንዲሁም ከሁለት ዓመት በፊት ከመንግስት ጋር የተደረሰውን ስምምነት በማክበር ህጋዊና ሰላማዊ ትግሉን የሚቀጥል መሆኑንና በዚህ የሰላማዊ ትግል ስትራቴጂ የማያምኑና የማያከብሩ አባላት የተለየ አቋም ይዘው ከድርጅቱ ጋር መቀጠል የማይችሉ መሆንናቸውን እያሳወቅነ መስሏቸው ወይም በስሜት የተሳሳተ አቋም የያዙ አባላት ወደ ትክክለኛው መስመር አንዲመለሱ አናሳስባለን።.
በትጥቅ ትግል ተሰማርተው ከሜዳ ያልገቡ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አባላትም ከመንግስት ጋር በሰላማዊ መንገድ ተነጋግረው ወደሰላማዊ እና ህጋዊ ትግል እንዲቀላቀሉ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
5. ከኣንድ ወር በፊት ጀምሮ የኦነግ ከፍተኛ አመራርን “ከሃዲ” “ጠላት” እና የመሳሰሉ ስሞችን በመለጠፍ አንዲሁም አገሪቷን አየመራ ካለው ፓርቲ ጋር ተቀላቅለዋል በማለት ሲነዛ የቀየውና አየተነዛ ያለው ርካሽ አሉባልታ አንደተለመደው ራስን ኣቻ የማይገኝለት ታጋይና ጀግና አስመስሎ ለማቅረብ ታስቦ መሆኑና በድርጅቱ ውስጥ ለዓመታት የቆዩት ብሹ አሰራሮች አውነታው እንዳይወጣ በመሸፋፈን ለእውነት የሚታገሉትን ታጋዮች ስም ለማጉደፍ እየተደረገ ያለ የፖለቲካ ሴራ በመሆኑ የኦሮሞ ህዝብ እውነታውን ለይቶ አንዲረዳ አናስገነዝባለን።
ለሚነዙ ውዥንብሮችና የሀስት ውንጀላዎች ሁሉ ምንጩ አቶ ዳዉድ ኢብሳ መሆናቸውን በድጋሚ አንገልጻለን። ቀደም ሲል የኦነግ አመራር የሚታወቀው እውነትን መናገርና በተዓማኒነታቸው ነው። በአቶ ዳዉድ የአመራር ዘመን ግን የሴራ ፖለትካ በድርጅቱ ውስጥ የተንሰራፋ በመሆኑ ይህን ከድርጅቱ በማጽዳት የድርጅቱን ዝና ወደ ነበረበት ለመመለስ በቁርጠኝነት እንታገላለን፣ የድርጅቱ አባላትና ደጋፊዎችም ለዚህ እንዲሰሩ ጥሪ አናቀርባለን።
6. የአንድ መሪ ጥንካሬ ትግልን ቋሚ ስራው በማድረግ የሚመዘን አይደለም። የወቅቱን ተጨባጭ ሁኔታ በመረዳትና ትግሉን ወደፊት ሊያራምድ የሚችል ሃሳብ የሚያመነጭ አመራር ማስገኘት ወሳኝ ነው። ።
ይህም ሊሳካ የሚችለው አሳታፊ፡ ዲሞክራሲያዊና ከሁሉም የኦሮሚያ የምርጫ ወረዳዎች የተወከሉ አባላት የሚሳተፉበት ጠቅላላ ጉባዔ እውን ማድረግ ሲቻል ብቻ ነው። ስለሆነም ኦነግ የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ በመጋቢት ወር 2012 ያስተላለፈውን ውሳኔ መሰረት በማድረግ ጠቅላላ ጉባዔው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ እንዲደረግ በቁርጠኝነት በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።
ስለዚህ በተለያዩ ቦታዎች የምትገኙ ነባር የድርጅቱ አባላትና ታጋዮች፡ በተለያዩ ምክንያቶች ከድርጅቱ የራቃችሁ፡ የተገፋችሁና የተረሳችሁ አባላት ለታሰበው ጉባዔ መሳካት የበኩላችሁን ድርሻ አንድትወጡ የትግል ጥሪ አናስተላልፍላችኋለን።
7.የኦሮሞ ነጻነት ትግል ከውስጥና ከውጭ የገጠሙትን ችግሮችና ያለበትን ድክመት በማስወገድ ትግሉን ኣጠናክሮ የኦሮሞን ህዝብ አንድነት ለማስቀጠል ከተለያዩ የኦሮሞ የህብረተሰብ ክፍሎች ፣ ነባር የድርጅቱ ታጋዮች፡ የሃይማኖት መሪዎች፡ ምሁራን፡ አባ ገዳዎችና ወጣቶች የሚያካትት የጋር ምክክር (Intra Oromo dialogue) መድረክ ለማዘጋጀት በሚደረገው እንቅስቃሴ ኦነግ የበኩሉን አስተዋጽዎ ያበረክታል።
የኦሮሞ ነጻነት ትግል ለአንድ ድርጅት ብቻ የሚተው ሳይሆን ሁሉም ዜጋ ሊሳተፍበት የሚገባ ብሔራዊና ህዝባዊ ትግል ነው።
ህዝባችንም ይህንን በመገንዘብ በሰላማዊ መንገድ የሚደረገውን ትግል በማጠናከርና በማጎልበት የኦሮሞ ብሄራዊ መግባባትን እውን ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት አንዲተባበር ጥሪያችንን አናስተላልፋለን።
8. ብዙ አመታት ባስቆጠረው የኦሮሞ ነጻነት ትግል ውስጥ ኦነግ ከተለያዩ ብሄርና ብሄረሰቦች ትግል ጋር የትግል አጋርነትና ወዳጅነት ለመፍጠር ጥረቶች ኣድርጓል። ይህም የትግል አጋርነትና ወዳጅነት በእኩልነት፡ በመከባበርና በዲሞክራስያዊ መርህ ላይ መሆንን መሰረት ያደረገ ነው።
ለታክቲክ ወይም ለግዜያዊ ጥቅም ተብሎ የሚደረግ ትብብር ዘለቄታዊ ጥቅም አያስገኝም። በተለይም ሕወሃት በኦሮሞ ህዝብና በኦሮሞ ታጋዮች ላይ ላደረሰው ከፍተኛ ጉዳት ይቅርታ ጠይቆ በኦሮሞ ህዝብ ቅቡልነት አስኪያገኝ ድረስ ኦነግ ከዚህ ድርጅት ምንም አይነት ግንኙነት የሌለው መሆኑን በድጋሚ እያሳወቅነ አቶ ዳዉድ ኢብሳ ከአመራሩ ዕውቅና ውጪ የፋይናንስ ሰራተኛውን ባለፈው ጊዜ መቐሌ በተካሄደው የህወሃት ስብሰባ ላይ አንዲሳተፍና ግኑኘት ለማድረጉ መላኩ የድርጅታችንን ፖሊሲ የጣሰ ህገ ወጥ ድርጊት መሆኑን መግለጽ እንፈልጋለን። ይህ በእንዲህ እያለ ኦነግ በኦሮሞና በትግራይ ህዝብ መካከል ያለው ወንድማዊና ዘላቂ ግንኙነት አንዲጠናከር ይሰራል።
9. በመጨረሻም የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ድርጅቱ ከተጋረጠበት አደጋ ለመታደግና ያለውን ድክመት ለማረም የሚሰራ መሆኑ እያሳወቀ የኢትዮጵያ ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ ከድርጅታችንና ከአገሪቱ የፓርቲ ህግና ደንብ ውጪ እየተንቀሳቀሱ ያሉትን የአቶ ዳዉድ ኢብሳ ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን አንዲከታተል እያስገነዘብን የኦነግ ሊ/መንበር የሚል ስም በመጠቀም ከቦርዱና ከተለያዩ አካላት ጋር ግኑኘት ለማድረግ የሚያደርጓቸው ጥረቶች በድርጅታችን ዘንድ ተቀባይነት እንደሌለው ደግመን እናሳውቃለን። የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ጠቅላላ ጉባዔ ተደርጎ አዲስ መሪ ኣስኪመረጥ ድረስ የድርጅቱ ተወካይና መሪ ምክትል ሊ/መንበሩ አቶ አራርሶ ቢቂላ እንደሆኑ በድጋሚ እናሳውቃለን።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር