በህንድ በአንድ ቀን ብቻ ከ90 ሺህ በላይ ሰዎች ላይ የኮሮና ቫይረስ ተገኘ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በህንድ በአንድ ቀን ብቻ ከ90 ሺህ በላይ ሰዎች ላይ የኮሮና ቫይረስ መገኘቱን የሀገሪቱ ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
ይህ ቁጥርም በሀገር ደረጃ እስካሁን በአንድ ቀን በዓለማችን ላይ የተመዘገበው ከፍተኛ ቁጥር ሆኗል ነው የተባለው።
የህንድ የጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፤ በ24 ሰዓታት በተደረገ የላቦራቶሪ ምርመራ በ90 ሸህ ሰዎች ላይ ቫይረሱ የተገኘ ሲሆን፥ ይህም ቫይረሱ በሀገሪቱ ከተከሰተ ወዲህ በአንድ ቀን የተመዘገበው ከፍተኛ ቁጥር ነው ተብሏል።
በአሁኑ ሰዓት በአጠቃላይ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 4 ነጥብ 11 ሚሊየን የደረሰ ሲሆን፥ ከእነዚህም ውስጥ የ70 ሺህ 626 ሰዎች ህይወት አልፏል ነው የተባለው።
በህንድ በየእለቱ እየተመዘገበ ያለው የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር ሀገሪቱን ከፍተኛ የተጠቂዎችን ቁጥር ይዛ ከዓለም ሁለተኛ ላይ ወደተቀመጠችው ብራዚል አነድትጠጋ እያደረጋት ነው።
በሀገሪቱ በየእለቱ የሚመዘገበው የተጠቂዎች በዚሁ ከቀጠለም በቀጣይ 24 ሰዓታት ውስጥ ብቻ ብራዚልን በማለፍ ከፍተኛ የተጠቂዎች ቁጥርን ከያዘችው አሜሪካ በመቀጠል ከዓለም ሁለተኛ ትሆናለች ነው የተባለው።
የቫይረሱ ስርጭት መጠን በዚሁ ከቀጠለም የደቡብ እሲያዊቷ ሀገር ህንድ እስከ ፊታችን መስከረም ወር መጨረሻ ድረስ አሜሪካንም በመብለጥ በቫይረሱ ክፉኛ ተጎጂ ሀገር ትሆናለች ሲሉም ባለሙያዎች ይተነብያሉ።
ምንጭ፦ aa.com
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።