በአማራ ክልል ወጣቶች በተገቢው መንገድ ለስራ ዕድል ፈጠራ የሚሆን ብድር እያገኘን አይደለም ሲሉ ቅሬታ አቀረቡ
አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 29፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ወጣቶች በተገቢዉ መንገድ ለስራ ዕድል ፈጠራ የሚሆን ብድር እያገኘን አይደለም ሲሉ ቅሬታ አቅርበዋል፡፡
ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ለወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ የፌዴራል መንግስት 3 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በአማራ ክልል ለሚገኙ ወጣቶች እና ስራ ፈላጊዎች ተሰራጭቶ ወደ ስራ ገብተው ቆይተዋል፡፡
ይህ ተዘዋዋሪ ፈንድ ወጣቶችን በማደራጀት እና ብድር በመስጠት ሂደት ልክ ተግባራዊ እየሆነ አለመሆኑን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገርናቸው ወጣቶች ይናገራሉ፡፡
በክልሉ ቴክኒክ ሙያ እና ኢንትርፕራይዝ ልማት ቢሮ የገቢያ ልማት እና ግብይት ዳይሮክቴሬት ተወካይ አቶ መኳንንት እማኙ በበኩላቸው በክልሉ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ለበርካታ ወጣቶች የተዘዋዋሪ ብድር ተሰቶ በስራ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በ 2009 3 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ለ50 ሺህ 623 ወጣቶች ብድር ተሰጥቶ 1 ቢሊየን ብር የሚሆነው እስካሁን ተመልሷል ነው ያሉት፡፡
በ2012 በጀት አመት ደግሞ ለ3 ሺህ 822 በላይ ወጣቶች ከ333 ሚሊየን ብር በላይ ብድር ተሰጥቷል ብለዋል፡፡
ወጣቶች በተለያዩ የስራ መስኮች ተሰማርተው ራሳቸውን ብሎም ሃገራቸውን ተጠቃሚ እንዲያደረጉ ከአማራ ብድር እና ቁጠባ ተቋም ጋር ውል እንዲወስዱ ተደርጎ እንደ ስራ ባህሪ ብድር እንዲመልሱ ይደረጋል ነው የሚሉት ።
የአማራ ብድር እና ቁጠባ ተቋም በበኩሉ የተዘዋዋሪ ብድር ፈንዱ በራሱ ችግር የነበረበት እና ስራ እድል ፈጠራን መሰረት ያደረገ እንዳልነበረ በመግለፅ በወቅቱ ከፌዴራል መንግስት 2 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር እና ከተቁሙ 600 ሚሊየን ብር በአጠቃላይ 3 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ብድር መሰጠቱን አስታውቋል።
ሆኖም ብድራቸውን ያልመለሱ ማህበራት መኖራቸውን የተናገሩት ዋና ስራ አስፈጻሚው አቶ መኮንን የለውምወሰን የተበደሩትንም ገንዘብ ሙሉ ለሙሉ በመመለስ የሚጠቀሱ ማህበራት መኖራቸውን ይናገራሉ ።
ሆኖም ይህንን ለመቆጣጠር የተመደበው አካል ስራውን በአግባቡ ባለመስራቱ ችግር ሊፈጠረ ችሏል ያለው ተቋሙ ይህ ደግሞ ለሌሎች አዳዲሰ የስራ እድል ለማግኘት በሚጥሩ ወጣቶች ላይ ተፅዕኖውን የጎላ መሆኑ ጠቁሟል።
ባለፈው በጀት ዓመት ለ3 ሺህ 800 ወጣቶች ብቻ በክልሉ ብድር የተሠጠው ተዘዋዋሪ ብድሩ መመለስ ከነበረበት ዝቅተኛ በመሆኑ ምክንያት ተብሏል።
ይህን ለማስተካከል በመደበኛ በመንግስት በጀት ብድር ቢመቻችም አብዛኛዎቹ ወጣቶች ግን መደበኛውን በጀት ለመበደር ፍላጎት እንደሌላቸው ተነግሯል።
በምንይችል አዘዘ