የብልፅግና ፓርቲ የፌዴራል አመራሮች ስልጠና በአዲስ አበባ መካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 25፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የብልጽግና ፓርቲ ፌዴራል ዞን አመራሮች ስልጠና \በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።
የአመራሩ ስልጠና ለተከታታይ አምስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን፥ በፌዴራል መዋቅር ውስጥ ከሚኒስትር እስከ ምክትል ዳይሬክተር ያሉ ከ420 በላይ አመራሮች ይሳተፋሉ።
በብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማህበራት ጉዳዮች ዘርፍ ሃላፊ ዶክተር አለሙ ስሜ በመክፈቻ ስነስርዓት እንዳሉት፥ ስልጠናው ለውጡን በማስቀጠል አገራዊ ብልፅግናን አውን ማድረግ የሚያስችል አቅም መፍጠር ያለመ ነው ብለዋል።
ስልጠናው አመራሩ የጠራ አስተሳሰብ ይዞ ለጋራ አላማ በጋራ እንዲሰረ ለማድረግ ያለመ መሆኑንም አመላክተዋል።
በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ብልጽግና ፓርቲ ቅርጫፍ ጽህፈት ቤት ለከተማዋ ከፍተኛ አመራሮች ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ 5 ቀናት የሚሰጠው የመጀመሪያ ዙር ስልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል ።
በስልጠናው መክፈቻ ፕሮግራም ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንደገለጹት፥ ብቃት ያለው አመራር ለማፍራት ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የተለያዩ ስልጠናዎች ሲሰጥ መቆየቱን ገልፀዋል።
አመራሩ የተለያዩ ችግሮችን በመሻገር ለህብረተሰቡ ፣ ለመንግስትና ለፓርቲው ጠቃሚ ተግባራትን እንዲፈጽም የአቅም ማጎልበት ተግባሩ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንና ዛሬ ላይ ሀገራቱ ብሎም ከተማዋ በድል የታጀቡ ለውጦች ላይ መድረሷን አስረድተዋል ።
በቀጣይም አመራሩ የህግ የበላይነትንና ሰላምን ማረጋገጥ እንዲሁም ህገ ወጥነትን አስቀድሞ መከላከል ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ እንዳለበት ገልጸዋል።
የስልጠናው አላማ ከመድረኩ እንደተገለጸው በአመራሩ እና በአባሉ መካከል የተግባርና የአመለካከት አንድነት መገንባት፣ ብልጽግናን እውን የሚያደርግ ጠንካራ ፓርቲና መንግስት መገንባት እና የተጀመረውን ሀገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሆነ ተገልጿል ።
በዛሬው ዕለት የተጀመረው ለ5 ቀናት የሚሰጠው የከፍተኛ አመራሩ ስልጠና በ2 ክላስተር ለ914 አመራሮች የሚሰጥ ሲሆን፥ በቀጣይ ጊዜያትም በሁለተኛ ዙር ቀሪ የከተማዋ አመራሮች እንደሚሰለጥኑ ታውቋል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።