Fana: At a Speed of Life!

የመገናኛ ብዙሃን ፖሊሲ የሚዲያ ዘርፉን ለማሳደግና አቅምን ለመገንባት አስቻይ ሁኔታን የሚፈጥር መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሚኒስትሮች ምክር ቤት በስራ ላይ እንዲውል የተወሰነው የመገናኛ ብዙሃን ፖሊሲ የሚዲያ ዘርፉን ለማስፋፋት፣ ለማሳደግ፣ ለመደገፍና አቅምን ለመገንባት አስቻይ ሁኔታን የሚፈጥር ነው ተባለ።

የብሮድካስት ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ የወንድወሰን አንዷለም ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ የመገናኛ ብዙሃን ፖሊሲው ሚዲያው ለሀገር ማበርከት ያለበትን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የጎላ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል።

እንደ ምክትል ዳይሬክተሩ ወንድወሰን አንዷለም ገለፃ፥ የሚዲያ ዘርፉ በፖሊሲ ማእቀፍ ያለመመራት በበዙ ችግሮች እንዲተበተብ አድርጎት ቆይቷል።

ማንም እንደፈለገ አፍራሽ እና ልክ ያልሆኑ እሳቤዎች የሚዲያ ዘርፉን መርህ ባልተከተለ መልኩ ሲያንሸራሽርበት መቆየቱንም ይናገራሉ።

እንደ አቶ የወንዶሰን አንዷለም ገለጻ፥ አዲሱ የሚዲያ ፖሊስ  በአጠቃላይ የሚዲያ ዘርፉን ለማስፋፋት፣ ለማሳደግ፣ ለመደገፍና አቅምን ለመገንባት አስቻይ ሁኔታን የሚፈጥር ነው ብለዋል።

ትውልደ ኢትዮጵያዊያንም የመገናኛ ብዙሃን ባለቤት የሚሆኑበትን ዕድልን የሚሰጥ መሆኑንም አስታውቀዋል።

22 ዋና ዋና ሐሳቦች የተካተቱበት ፖሊሲው የመገናኛ ብዙሃን ነፃነትን የሚጠብቅ፣ ተጠያቂነት እንዲኖር የሚያደርግ እንዲሁም የኢኮኖሚ አቅማቸው እንዲጎለብት የሚያስችል ነው ሲሉም ገልጸዋል።

የመገናኛ ብዙሃን ባለቤትነት፣ የመገናኛ ብዙሃን መሰረተ ልማት፣ ብዝሃነት፣ ስብጥርና አመራርንም በተመለከተ ፖሊሲው ሊተገበሩ የሚገባቸውን አካሔዶችን መፈተሹን አመልክተዋል።

በተጨማሪም ሃይማኖታዊ መገናኛ ብዙሃንም ለመጀመሪያ ጊዜ በፖሊሲው የተካተቱና ተመዝግበው ፈቃድ የሚያገኙ ሲሆን፥ እስካሁን የነበሩት ሕጎች እውቅና የሚሰጧቸው ስላልነበሩ ሕግና ስርአትን ጠብቀው እንዲሰሩ ይደረጋል ነው ያሉት።

ፍትሐዊ የሃብት ክፍፍል በንግድና በሕዝብ መገናኛ ብዙሃን መካከል እንዲኖር ለማድረግ የመንግስት ማስታወቂያዎችም በእኩል ደረጃ መሰራጨት እንዲችሉ አቅጣጫ ማስቀመጡንም ገልጸዋል።

መገናኛ ብዙሃን የኢኮኖሚ ጫና እንዳይደርስባቸው በፖሊሲው የተቀመጡ ነጥቦች መኖራቸውን፤ የሕትመት ዋጋ የሚቀንስበትና ተሳትፏቸው የሚጎለብትበት ሁኔታ መኖሩንም አመልክተዋል።

በቀጣይነትም የሚወጡ ዝርዝር መመሪያና ሕጎች እንደሚኖሩም ምክትል ዳይሬክተር አቶ የወንድወሰን አንዷለም ተናግረዋል።

በአፈወርቅ አለሙ

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.