Fana: At a Speed of Life!

ብሔራዊ  መረጃና ደህንነት አገልግሎት  ሽብርተኝነትንና ህገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርን  በመግታት  አገራዊ ህልውናን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሚና ማበርከቱ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት  ሽብርተኝነትንና ህገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርን  በመግታት  አገራዊ ህልውናን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሚና ማበርከቱ ተገለጸ።

ብሔራዊ  መረጃና ደህንነት አገልግሎት በተጠናቀቀው የ2012 የበጀት  ዓመት በአገርና ህዝብ ላይ ቢቃጡ የደህንነት ስጋት የሚፈጥሩና  በብሄራዊ  ጥቅም ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ  የሽብር ጥቃቶች  እንዲመክኑ እንዲሁም  በአገር ውስጥ ቢሰራጩ ግጭትን ሊያባብሱ የሚችሉ ህገ-ወጥ የጦር መሣሪያዎች  በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ በማድረግ  አገራዊ ህልውናን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ሚና ማበርከቱን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ አመልክቷል፡፡

አገልግሎት መስሪያ ቤቱ የተቋሙን የስራ አፈጻጸም አመታዊ ግምገማ አስመልክቶ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፥ በ2012 በጀት ዓመት አልሸባብና አይኤስ ከምስራቅ አፍሪካ በመነሳት ኢትዮጵያን ዒላማ ያደረጉ እንቅስቃሴዎችን  ሲያከናውኑ ነበር።

የሽብር እንቅስቃሴውን ለመግታት በተከናወነው ጥብቅ ሙያዊ ክትትል እንዲሁም ከሌሎች አቻ ተቋማት ጋር  በተደረገው የመረጃ ልውውጥ  የሽብር ሴራዎቹን ማክሸፍ ተችሏል ብሏል መግለጫው።

በቀጠናው እያደገ የመጣው የሽብርተኝነት እንቅስቃሴ በአገር ብሄራዊ ደህንነትና ጥቅም ላይ ጉዳት እንዳያስከትል ከሌሎች የአገሪቱ የፀጥታና መረጃ ተቋማት ጋር በመናበብ በተወሰደው እርምጃ በ2012 ዓ.ም በቁጥጥር ሥር ከዋሉት 16 የአልሻባብና  17 የአይኤስ በድምሩ 33 አሸባሪዎች የጥፋት ተልዕኳቸውን ለመፈጸም ኢላማ ካደረጓቸው ተቋማት ፎቶግራፎችና ሰነዶች ጋር እንዲሁም ለጥፋት ተልዕኮቸው ሊጠቀሙባቸው ካዘጋጆቸው የፍንዳታ ቁሶች ጋር  በቁጥጥር ሲል እንዲውሉ ማድረጉ ይታወሳል።

በተያያዘ አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ የሽብር እንቅስቃሴ ሊያባብሱና ስርዓት አልበኝነትን በማስፈን በህዝቡ ሰላምና ደህንነት ላይ ስጋት ሊደቅኑ የሚችሉ ህገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውሮችን ከመከላከልና ከመቆጣጣር አንጻርም፤ 499 ክላሽንኮቭ  ጠመንጃዎች27 ሺህ 237 ሽጉጦች፣ 11 ቦንቦች8 መትረየስ ጠመንጃዎች፣ 168 ሺህ 241  ጥይቶች እንዲሁም 59 የጦር መሣሪያ አዘዋዋሪዎች  በቁጥጥር ሥር  እንዲውሉ የማድረግ ስራዎችን አከናውኗል።

በተለይ ከቱርክ ተነስተው በጅቡቲ ወደብ በኩል ወደ ኢትዮጵያ የገቡትና በቁጥጥር ሥር የዋሉት ግምታቸው ከ500 ሚልየን ብር በላይ የሆኑ 18 ሺህ  32 ሽጉጦች እና የተለያዩ የኤሌክትሮኒኪስ እቃዎች በህገ ወጥ መንገድ ገብተው በአገር ደህንነትና ሰላም ላይ ሊያስከትሉ ይችል የነበረው ሴራ ተቋሙ ባደረገው ጥብቅ ሙያዊ የመረጃ ስራ ማክሸፉ  ይታወሳል።

በቅርቡ አይኤስ እና አልሸባብ በኢትዮጵያ  ላይ የሽብር ጥቃት  ለመሰንዘር  መዛታቸውን የሚያሳዩ  የቪዲዮ መልዕክቶች  መልቀቃቸውን በመግለጫው ያመለከተው ብሔራዊ  መረጃና ደህንነት አገልግሎት፥ ይህንንም የሽብር አደጋ ለማክሸፍ የሚያስችል ስራ ሌትተቀን እየሰራ መሆኑን ገልጿል።

ህብረተሰቡም በአካባቢው ከተለመደው ውጭ የተለየ እንቅስቃሴ ሲመከለት ለሚመለከታቸው  የደህንነትና የጸጥታ አካላት ጥቆማ እንዲሰጥ ተቋሙ ጥሪ  አቅርቧል።

በመጨረሻም ተቋሙ በአመቱ የኢትዮጵያ ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ  ከህዝቡ ጋር ተቀናጅቶ የሰራቸውን ስራዎች በቀጣይ በተከታታይ የሚገልፅ መሆኑንም አስታውቋል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.