የመንግስት ዓላማ ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ንጋትን ማብሰር ነው – ጠ/ሚ ዐቢይ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የመንግስት ዓላማ ለእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ንጋትን ማብሰር ፤ ግቡም ለሁሉም ሕዝብ ብሩህ ቀን እንዲመጣለት ማስቻል መሆኑን አስታወቁ።
በፌስቡክ ገፃቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ የብልጽግና መንገድ የማለዳውን ጀምበር ተከትሎ እየፈካ መጥቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የብርሃን ጸዳሎቹ ሙቀትና ፍካትን እያጎለበቱ ለብዙዎች ተስፋን መፈንጠቃቸውን ቀጥለዋል ብለዋል።
እንዳንዱ ዜጋ በሀገሩ ደስታን፣ በሀገሩ ምቾትን፣ በሀገሩ ተስፋን እንዲጨብጥ የማድረግ ጉዞውም የማለዳዋን ፀሐይ ተከትሎ ሙቀትና ፍካቱ እየጨመረ ብሩህ የሆነው እኩለ ቀን ላይ ማድረስ ነው በማለትም ገልፀዋል።
በዚያ በቂ ሙቀት፣ በቂ ብርሃን፣ በቂ ምቾት እንዳለ በማንሳትም ከጨለማ ይልቅ ብርሃን እንደሚያዋጣ የሚረዳው ህዝብ ለጥፋት መንገድ ተጓዦች ጀርባውን ሰጥቶ ሙሉ አቅምና ጉልበቱን ወደ ሁለንተናዊ ብልጽግና እንደሚያደርግም ነው የገለጹት።