ሚኒስቴሩ በሲሚንቶ አቅርቦት በኩል እየተፈጠረ ያለውን ችግር ለመፍታት የሚያስችል የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በሲሚንቶ አቅርቦት በኩል እየተፈጠረ ያለውን ችግር ለመፍታት የሚያስችል የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ።
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ዛሬ በሰጡት መግለጫ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች መለዋወጫ ከውጭ ለማስገባት የሚገጥማቸውን የውጭ ምንዛሬ ለመቅረፍ 85 ሚሊየን ዶላር ተመድቧል ብለዋል።
ይህም በርካታ ፋብሪካዎች የማምረት አቅማቸው እስከ 20 በመቶ እንዲወርድ ያደረገውን የመለዋወጫ ችግር በመቅረፍ የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን የማምረት አቅም በአማካይ 63 በመቶ ጠብቀው እንዲቀጥሉ ያደረጋል ብለዋል።
በዚህም መጠን የሚመረተው ቢስተካከልም ሲሚንቶን ከፋብሪካዎቹ ወደ ተጠቃሚዎች የሚያደረሰው የግብይት እና ስርጭት ሂደት ከፍተኛ ችግር ያለበት ነው።
በዘርፉ ፍቃድ የሌላቸው ግለሰቦች ከፋብሪካው ጋር ባላቸው የግል ግንኙነት ምርቶችን በአዲስ አበባ ዙሪያ ከማስቀመጥ ጀምሮ የአየር ባየር ንግድ የሚስተዋልበት ነው።
ለፋብሪካዎቹ ቅድመ ክፍያ በመክፈል ኩፖን ከመቸርቸር አንስቶ በአቅርቦት እና ፍላጎት መካከል ያለው ልዩነት በገበያው እንዲሰፋ የማድረግ ህገ ወጥ ተግባራት መኖሩን ተረጋግጧል ነው ያሉት ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል።
በሰው ስራሽ መንግድ የሚፈጠረውን የሲሚንቶ እጥረት ለመቅረፍ ከቀጣይ ሰኞ ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግ የሲሚንቶ ግብይት መመሪያ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።
በተጨማሪም የፋብሪካዎቹ የሰው ሀይል አቅም እንዲያድግ እንዲሁም እያንዳንዱ የሲሚንቶ ፋብሪካ ያለበትን ችግር በጥናት በመለየት መፍትሄ እንዲቀመጥለት ተደረጓል።
ከትራንስፖርት እጥረት ጋር ያሉ ችግሮችን ለመፍታትም ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ጋር ንግግር መጀመሩንም ነው ሚኒስትሩ ያነሱት።
ለ1 ወር በሲሚንቶ ፋብሪካዎች ቆመው ይቆዩ የነበሩ ተሽከርካሪዎች በ2 ቀን ውስጥ ምርት ጭነው ከፋብሪካ እንዲወጡም ማድረግ ተችሏል።
በሀገሪቱ ለተፈጠረው የሲሚንቶ እጥረት በጥልቅ ጥናት መፍትሄዎቹ መቀመጡን የሚናገሩት ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል፤ መፍትሄዎቹም በአጭር፤ መካከለኛ እና በረጅም ጊዜ የዘርፉን ችግር ለመፍታት ተግባራዊ ይደረጋል።
ለሶስት ወራት የውጭ ምንዛሬ አካውንት ያላቸው የሃገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች ሲሚንቶን ከውጭ እንዲያስገቡም አንዱ እርምጃ ነው።
በረጅም ጊዜም በሃገር ውስጥ ያለውን ሲሚንቶ የማምረት አቅም ለመጠቀም የሃገር ውስጥ እና የውጭ ባለሃብቶች ወደ ዘርፉ እንዲቀላቀሉ የማድረግም ግብም ተቀምጧል።
ይሄም ከሃገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ለውጭ የማቅረብ እና አንድ የውጭ ምንዛሬ ማስገኛ መስክ እንዲሆንም ይደረጋል ብለዋል ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል።
በበላይ ተስፋዬ
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።