መካከለኛ እና አነስተኛ ኩባንያዎች ላይ ያነጣጠረ የሳይበር ጥቃት ዘመቻ ተከፍቷል-ካስፐርስኪ ላብ
አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 19 ፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ታዋቂው የሳይበር ደህንነት ምርቶች አቅራቢዉ ‘ካስፐርስኪ ላብ’ በተራቀቁና ቀጣይነት ባላቸዉ የመረጃ ጥቃቶች ላይ ባደረገዉ ጥናት መካከለኛና አነስተኛ ኩባንያዎችን ያነጣጠረ የሳይበር ጥቃት ዘመቻ መከፈቱን ገልጿል።
ካስፐርስኪ በሪፖርቱ ‘ዴዝስቶከር’ (DeathStalker) የተባለ የመረጃ መንታፊ ቡድን ከፍተኛ የሚባል የሳይበር ጥቃቶችን በመካከለኛ እና ዝቅተኛ ኩባንያዎች ላይ እያደረሰ መሆኑን ጠቅሷል።
የኩባያዎችን መረጃ በመመንተፍ የሚታወቀው ቡድኑ ከፈረንጆቹ 2012 ጀምሮ በዚህ ህገወጥ ተግባር ላይ ተሰማርቶ እንደሚገኝ ተገልጿል።
የመረጃ መንታፊ ቡድኑ በዋናነት የፋይናስ ተቋማን ኢላማ በማድረግ በትናንሽ እና መካከለኛ ኩባንያዎች ላይ በሳይበር ስለላ ዘመቻዎች እንደሚያከናውን ታውቋል።
በመሆኑም አነስተኛ፣ መካከለኛ እንዲሁም ግዙፍ የንግድ ድርጅቶች እና የመንግስት ተቋማት ከረቀቁ እንደ “ዴዝ ስቶከር” ከመሳሰሉ የመረጃ መንታፊዎችን ሚሰነዘርን ጥቃት ለመቋቋም ዝግጁ መሆን አለባቸው ሲል ካስፐርስኪ አሳስቧል።
የካስፐርስኪ ኩባንያ ከፈረንጆቹ 2018 ጀምሮ ባደረገው ክትትል “የዴዝ ስቶከር” እንቅስቃሴዉን ፓወር ሲንግ (Powersing) ኢቪልነም /Evilnum/ እና ጃኒኪዩብ /Janicub/ ከተባሉ የማልዌር አይነቶች ጋር ግንኙነት እንዳለዉ ጠቁሟል።
“የዴዝ ስቶከር” ተንኮል አዘል ፋይሎችን የያዙ ማህደሮችን ትክክለኛ የሆኑ እና የተለያዩ የማጥመጃ ኢ-ሜይል መልእክቶች አማካኝነት ጥቃቶችን የሚያደርስ መሆኑንም ገልጿል።
ተጠቃሚው አቋራጭ(‘shortcut) ፋይሉን በሚጭንበት ወቅት ሌላ ተጨማሪ ይዘቶች ከበይነ-መረብ ዳወንሎድ በመሆን የመረጃ መንታፊዎች የሳይበር ጥቃት ኢላማ የሆነውን አካል ኮምፒዉተር መቆጣጠር እንደሚያስችል ተነግሯል።
ከመረጃ መንታፊ ቡድኑ ጋር ንክኪ ያላቸዉ ዉስጥ “ከፓወርሲንግ” ጋር የተያያዙ የሳይበር ጥቃቶች በአርጀንቲና፣ በቻይና፣ በቆጵሮስ፣ እስራኤል፣ ሊባኖስ፣ ስዊዘርላንድ፣ ታይዋን፣ ቱርክ፣ ብሪታንያ እና ዩናይትድ አረብ ኢሚሬቶች የተከሰተ ሲሆን፥ “ከኢቪልኒየም” ጋር የተያያዙ ጥቃቶች ደግሞ ቆጵሮስ፣ ህንድ፣ ሊባኖስ፣ ሩሲያ እና ዩናይትድ አረብ ኢሚሬቶች ዓለም አቀፍ ጥቃቶች መገኘታቸው ተጠቅሷል።
ይህ አደገኛ የሳይበር ጥቃት እንቅስቃሴ በአነስተኛና በመካከለኛ ደረጃ ያሉ ኩባንያዎች በሳይበር ደህንነት አጠባበቅ እና በግንዛቤ ፈጠራ ስራ ላይ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ እንደሚያስፈልግ የሚያረጋግጥ ማስረጃ እንደሆነ ተጠቁሟል ፡፡
በኢትዮጵያም የዲጂታል ሲስተም ተጠቃሚዉ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱ ይታወቃል፡፡
ማህበረሰቡም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመጣዉ የዲጂታል ስርዓት አዳዲስ የጥቃት ተጋላጭ እንዳይሆን የጥንቃቄ ርምጃዎችን በተገቢዉ መንገድ በመተግበር በግለሰብ፣ በተቋም እንዲሁም በሃገር ላይ ሊደርሱ የሚችሉ የሳይበር ጥቃት አደጋዎች መቀነስ እንደሚገባ ከኢመደኤ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።