Fana: At a Speed of Life!

ቤቶች ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ በ3 ቢሊየን ብር ለሚያስገነባው ዘመናዊ መንደር ከተቋራጮች ጋር ስምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 15 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ ገርጂ በሶስት ቢሊየን ብር ለሚያስገነባው ዘመናዊ መንደር ከሃገር ውስጥና ከውጭ ተቋራጮች ጋር በዛሬው ዕለት ስምምነት ፈፅሟል።

ኮርፖሬሽኑ ስምምነቱን ኦቪድ ከተባለ ሀገር በቀልና ከደቡብ ኮሪያ ኩባንያዎች ጋር ሽርክና ካለው ኩባንያ ጋር ነው የገባው።

በስምምነቱ መሰረት በገርጂ መኖሪያ መንደር በሚቀጥሉት 18 ወራት ውስጥ 510 መኖሪያ ቤቶች የሚገነቡ ሲሆን፤ መኖሪያ ቤቶቹ ባለ 10 ወለል ህንጻ ይኖራቸዋል።

የመኖረያ መንደሩ ሲጠናቀቅ በከተማዋ የሚታየውን የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ችግር በተወሰነ መልኩ የሚያቃልል መሆኑን የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ረሻድ ከማል ተናግረዋል።

በቤቶቹ ግንባታ ወቅት አንድ የህንጻ ወለልን በአምስት ቀናት ውስጥ ሰርቶ የሚያጠናቅቅ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ ይውላል ተብሏል።

ሲ ኤም ሲ ከሚገኘው የኮርፖሬሽኑ የመኖሪያ መንደር ልምድ ተወስዶ በ3 ሄክታር ላይ የሚገነባው ይህ መንደር ሲጠናቀቅ ዘመናዊነትን የተላበሰ ቅንጡ የመኖሪያ መንደር ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

የመኖሪያ መንደሩ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ለመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ይውላል ነው የተባለው።

የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ከ28 ዓመት በኋላ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ወደ ቤቶች ግንባታ ራሱን በመመለስ በተለያዩ ስምንት የግንባታ ቦታዎች ቤቶችን እየገነባ መሆኑን የኢቢሲ ዘገባ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.