ለጎሃፅዮን – ደጀን መንገድ ዘላቂ መፍትሄ መስጠት የሚያስችል ጥናት እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 8 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን መልክዓ ምድራዊ አቀማመጡ አስቸጋሪ ለሆነው የጎሃፅዮን (ቀሬ ጎዓ) – ደጀን መንገድ ዘላቂ መፍትሄ መስጠት የሚያስችል ጥናት እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን በስፍራው ተጠባባቂ የራስ ሀይል ጥገና በማድረግ የትራንስፖርት ፍሰቱ እንዳይስተጓጎል እያደረገ ይገኛል።
ይሁን እንጅ መንገዱ ዘላቂ መፍትሄ እንደሚያስፈልገው በጥናት ተረጋግጧል።
የመንገዱን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት እንዲያስችልም የጃፓን ባለሙያዎች በቦታው ተሰማርተው ጥናት እያደረጉ መሆኑን አስታውቋል።
በባለስልጣኑ የዓለም ገና መንገድ አውታር እና ደህንነት ዳይሬክተር አቶ ዑመር ሁሴን፥ የአባይ በረሃ መንገድ በመሬት መንሸራተት ምክንያት በየጊዜው ለብልሽት እንደሚዳረግ ተናግረዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም ባለስልጣኑ ችግሩን ለመፍታት ከጃፓን ባለሙያዎች ጋር ጥናት እያደረገ ነው ብለዋል።
የጥናቱ ውጤት እንደተጠናቀቀም ሊወሰድ የሚችለው ዘላቂ መፍትሄ ለመንግስት ቀርቦ በቀጣይ ውሳኔ እንደሚያገኝ ከባለስልጣኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ከአዲስ አበባ ባህርዳርና ጎንደር የሚያገናኘው የአባይ በረሃ መንገድ በሚደርስበት የመሬት መንሸራተት ምክንያት በተደጋጋሚ ችግር ይገጥመዋል።