በፈረንጆቹ 2020 ሊጎበኙ ከሚገባቸው 50 የዓለማችን ቦታዎች መካከል አዲስ አበባ አንዷ ሆናለች
አዲስ አበባ ታህሳስ 8፣ 2012 (ኤፍቢሲ) በዓለም ላይ ታዋቂ የጉዞ መረጃ አውጪ ድረገፅ የሆነው ትራቨል ኤንድ ሌይዠር የተባለው ድረገፅ በፈረንጆቹ 2020 ሊጎበኙ ከሚገባቸው 50 የዓለማችን ስፍራዎች ውስጥ አዲስ አበባን አንደኛ አደርጎ አስቀምጣል።
የዘንድሮውን የሰላም ኖቤል ሽልማት የተቀበሉት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቤተመንግስት አስገንብተው በቅርቡ ለህዝብ ክፍት ያደረጉት አንድነት ፓርክ የከተማዋ አዲስ ገፅታ መሆኑን ድረገፁ አስነብቧል።
በተጨማሪም ጎብኚዎች የማስፋፊያ ግንባታ የተደረገለት ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ገና ሲደርሱ በከተማዋ ስላለው ለውጥ መመልከት ይችላሉም ነው ያለው።
ከዚያ ውጪ በአዲስ አበባ መካኒሳ አካባቢ የተከፈተው ዞማ ሙዚየም የዚህች የአፍሪካ መዲና የሆነች ከተማ ሌላ አዲስ ገፅታ እንደሆነም አመልክቷል።
ከአዲስ አበባ ቀጥሎም በፔሩ፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ኦስትሪያና ሜክሲኮ የሚገኙ የተለያዩ ስፍራዎች ከሁለት እስከ አምስት ደረጃን ይዘዋል።
ድረገፁ እነዚህን የዓለማችንን ሊጎበኙ የሚገባቸው ስፍራዎች ብሎ የዘረዘራቸውን አካባቢዎች ሲመርጥ፥ የተለያዩ ጸሁፎችን፣ የቱሪዝም ስታትስቲክስን፣ ዋና ዋና ክስተቶችን ፣ አዳዲስ የበረራ መንገድ ሰንጠረዦችን እና የሆቴል አገልግሎትን በማጥናት መሆኑን ጠቁሟል።