ርዕሳነ መስተዳድሮቹ ለፍቼ ጫምባላላ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦሮሚያ፣ የሶማሌ፣ የደቡብ ኢትዮጵያና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች ለሲዳማ ብሄር የዘመን መለወጫ ፍቼ ጫምባላላ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ባስተላለፉት መልዕክት፥ የፍቼ ጫምባላላ በዓል በሲዳማ ህዝብ ዘንድ በድምቀት የሚከበር በዓል መሆኑን ገልጸዋል።
የሁለቱን ክልሎች ህብረብሔራዊ ወንድማማችነት በማጠናከር የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ በጋራ መስራታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ፥ የሶማሌና የሲዳማ ህዝቦች ዘመናትን ያስቆጠረ ታሪካዊ ትስስር ያላቸው ወንድማማች ሕዝቦች በመሆናቸው የፊቼ ጫምባላላ በዓልም እንደ ራሳችን የምንቆጥረው የጋራ በዓላችን ነው ያሉት፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በበኩላቸው፥ ፍቼ ጫምባላላ ከብሔሩ አልፎ የመላው የሰው ልጆች ወካይ የማይዳሰስ ባሕላዊ ቅርስ ሆኖ በዩኔስኮ መመዝገብ የቻለ የሀገራችን የጋራ ሃብት ነው ብለዋል፡፡
የሁለቱን ክልሎች ህዝቦች የጠበቀ ባህላዊ፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር በማጎልበት የጋራ ልማትንና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በዓሉ ያለው አንድምታ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት፥ ፍቼ ጫምባላላ የኢትዮጵያን ብዝሃ ማንነት ከሚመሰክሩ አብነቶች አንዱ መሆኑን አውስተዋል፡፡