Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ 165 ሺህ ዜጎች የ5 ሚሊየን ኮደርስ የስልጠና መርሐ-ግብርን እየተከታተሉ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ 165 ሺህ ዜጎች የ5 ሚሊየን የኢትዮ ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ስልጠና መርሐ-ግብር እየተከታተሉ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ገለጸ፡፡

የቢሮው ምክትል ኃላፈ ቱሉ ጥላሁን (ዶ/ር) ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ በከተማ አስተዳደሩ በሶስት ዓመት ውስጥ ከ300 ሺህ በላይ ዜጎች የ5 ሚሊየን ኮደርስ የስልጠና መርሐ ግብር እንዲከታተሉ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል፡፡

ዕቅዱን ለማሳካት ስለስልጠናው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን በመፍጠር ወደ ስራ መገባቱን የገለጹት ኃላፊው÷ አሁን ላይ ከ165 ሺህ በላይ ዜጎች ስልጠናውን እየተከታተሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ 56 ሺህ ዜጎች ስልጠናውን በማጠናቀቅ የምስክር ወረቀት መውሰዳቸውንና የ5 ሚሊየን ኮደርስ የስልጠና መርሐ ግብርን ለማሳካት የሚደረገውን ጥረት በቀዳሚነት እያከናወነ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

ስልጠናውን ለኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ተማሪዎች ብቻ እንደሚሰጥ ተደርጎ የሚወሰድ የተሳሳተ ግንዛቤ መኖሩን የጠቆሙት ቱሉ (ዶ/ር)÷ ስልጠናውን ያለ ዕድሜ እና ፆታ ልዩነት ሁሉም ሰው መውሰድ እንደሚችል አስገንዝበዋል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ580 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውን የ5 ሚሊየን ኮደርስ የስልጠና መርሐ ግብር እየተከታተሉ ሲሆን÷ ከ180 ሺህ በላይ ዜጎች ደግሞ ስልጠናውን በማጠናቀቅ የምስክር ወረቀት መውሰዳቸውን የኤኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.