ፍቼ ጫምባላላ ለሀገራዊ መግባባት…
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል ‘ፍቼ ጫምባላላ’ ከዛሬ ጀምሮ በልዩ ልዩ ባህላዊ ሁነቶች በድምቀት ይከበራል።
የፍቼ ጫምባላላ እሴቶች ለሀገራዊ መግባባት፣ ለህዝብ አንድነትና ለሰላም ጉልህ አበርክቶ እንዳላቸው የሲዳማ ክልል የባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ የቱሪዝም ዘርፍ ኃላፊ አቶ አበበ ማሪሞ ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል፡፡
የበዓሉ የእርቅ፣ የሰላምና የአንድነት እሴቶች በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይደሳስ ቅርስ ሆኖ ከ10 ዓመታት በፊት ለመመዝገብ እንዳበቃው አስታውሰዋል፡፡
የበዓሉ ዝግጅት አካል የሆነው ‘ኡሱራ’ የተሰኘው፣ የሲዳማ ብቁ አረጋዊያን (ጭሜየ) የሚይዙት የጾም ስርዓት፣ ከበዓሉ ቀደም ብሎ ባሉ ቀናት የሚከናወን ሲሆን፥ ይህም ስላለፈው በደል ንስሃ የሚገባበትና መጪው ጊዜ የሰላም እንዲሆን የመማጸኛ ወቅት ነው፡፡
ኡሱራ የተጣሉ ሰዎችን የማስታረቅ ስራ የሚከናወንበት የእርቅ ስነ-ስርዓት ጭምር በመሆኑ ሰዎች ተጣልተው ወደ አዲስ ዘመን መሸጋገር የለባቸውም በሚል እሳቤ የሚፈጸም ነው፡፡
የእርቅ ስነ-ስርዓቱ ‘አፊኒ’ የተሰኘው የሲዳማ የውይይት ባህል የሚገለጥበት ሁነት እንደሆነ አቶ አበበ ማሪሞ አስረድተዋል።
እርቅ፣ ውይይትና ፍትህን አቅፎ የያዘው አፊኒ በዳይና ተበዳይ ሀሳባቸውን የሚናገሩበትና ለመደማመጥ ትልቅ ቦታ ያለው ስርዓት መሆኑንም ገልጸዋል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአፊኒ ስርዓት ለመግባባትና ለእርቅ ያለውን አበርክቶ በመገንዘብ ለሚያከናውናቸው የምክክር ተግባራት እንደ አንድ ግብዓት አድርጎ መውሰዱን ጠቅሰዋል።
በዓሉ ከእርቅ እሴትነቱ ባሻገር የሰላምና የአንድነት በዓል መሆኑን ገልጸው፤ ሰላም የፍቼ ጫምባላላ አስኳል ነው ብለዋል።
ጭሜየ በመባል የሚታወቁት ሽማግሌዎች ከበዓሉ ቀደም ብሎ ኡሱራ የተሰኘዉን ፆም በመግባት ለሀገር፥ ለህዝብና ለእንስሳት ጭምር ሰላም እንዲሰፍን ፈጣሪን ይማፀናሉ።
ፍቼ ጫምባላላ የአብሮነትና የአንድነት በዓል እንደመሆኑ ወንድ ሴት፣ ህጻን አዛውንት፣ ሀብታም ድሃ ሳይባል ሁሉም በጋራ ያከብረዋል።
አቶ አበበ ማሪሞ እንደሚሉት፥ በዓሉ በሲዳማ ህዝብ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም ጭምር ተናፍቆ የሚጠበቅ በዓል ነው።
የሲዳማ ክልል አጎራባች አካባቢዎች ህዝብ በዓሉን በጋራ የሚያከብሩትና የጋራ እሴት በማዳበር የባህል ልውውጥ የሚደረግበት ትልቅ ሁነት መሆኑን ተናግረዋል።
በዓሉ ለአካባቢ ጥበቃ ያለው አስተዋፅዖ በዩኔስኮ ቅርስነት እንዲመዘገብ ካስቻሉት እሴቶች አንዱ ነው።
በፍቼ ጫምባላላ ዛፍ አይቆረጥም፣ ከብት አይታረድም እንደውም በአዲስ የግጦሽ ሣር ይለቃሉ፣ መሬት አይቆፈርም፥ አደን ስለማይታደን ሁሉም ተፈጥሮ ይከበራል፣ ያርፋል።
የሲዳማ ብሄር የዘመን መለወጫ ‘ፍቼ ጫምባላላ’ ባህላዊ ስርዓቱን ጠብቆ በልዩ ልዩ ሁነቶች ከዛሬ ጀምሮ ይከበራል።
አይዴ ጫምባላላ!
በኃይለማርያም ተገኝ