Fana: At a Speed of Life!

በቀደሙት የመሬት ሳተላይቶች የታዩ ውስንነቶችን የምትቀርፈው ‘ETRSS-2’ የመሬት ምልከታ ሳተላይት

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በቀጣዩ ዓመት ወደ ህዋ ለማምጠቅ በውጥን የያዘቻት ‘ETRSS-2’ የመሬት ምልከታ ሳተላይት በቀደሙት የመሬት ሳተላይቶች የታዩ ውስንነቶችን እንደምትቀርፍ የስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ገለፀ፡፡

የመሬት ምልከታ ሳተላይቶች፤ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቆጣጠር፣ ለአደጋ ጊዜ ምላሽ እና አያያዝ፣ ከግብርና ጋር የተያያዙ ጥናት እና ምርምሮችን ለመሥራት ብሎም ለሌሎች ጉዳዮች ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ይታወቃል፡፡

ኢትዮጵያም ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም ለማግኘት ለመጀመሪያ ጊዜ ‘ETRSS-1’ የተሰኘችውን የመሬት ምልከታ ሳተላይት በ2012ዓ.ም ታኅሣስ ወር ላይ ወደ ህዋ መላኳ ይታወሳል፡፡

በ2013ዓ.ም ደግሞ ከመጀመሪያዋ ሳተላይት በምስል ጥራቷ የተሻለች ኢቲስማርት አር ኤስ ኤስ የተባለች ሳተላይት ወደ ህዋ ማምጠቋ ይታወቃል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር በላቸው ፀሐይ እንዳሉት፤ የመጀመሪያዋ ሳተላይት ለ3 ዓመት ተኩል ሁለተኛዋ ደግሞ ለ1 ዓመት በነበራቸው የህዋ ቆይታ ለደንና አየር ንብረት ጥበቃ ብሎም ለአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ- ግብር የጎላ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡

ከሳተላይቶች በተገኙ ምስሎችም የተራቆቱ አካባቢዎችን በመለየት በደን መሸፋን መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል በሁለቱ የመሬት ምልከታ ሳተላይቶች የታዩ ውስንነቶችን እንደምትቀርፍ የታመነባት 5 ዓመት ያገልግሎት ጊዜ ያላት ETRSS-2 የመሬት ምልከታ ሳተላይት አልምቶ ወደ ትግበራ ለመግባት ከቻይና ኩባንያ ጋር የውል ስምምነት መፈረሙን አውስተዋል፡፡

ሳተላይቷ የዕይታ መጠኗ ከፍ ያለ እና ከቀደምቶቹ በተሻለ የሰብል፣ የደን እና የውኃ ክትትልና ቁጥጥር ማዕከላት እንዲሁም የጎርፍ፣ የመሬት መንሸራተትና የተፈጥሮ አደጋ ስጋት መከላከል ማዕከላት ውሳኔ ሰጭነት እና ለፖሊሲ ቀረጻ ድጋፍ ለመስጠት ወቅታዊ መረጃ ትልካለች ተብሎ ተስፋ ተጥሎባታል፡፡

በፌቨን ቢሻው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.