ኢትዮጵያ እና ኬንያ በጉምሩክ ጉዳዮች ላይ በጋራ በሚሠሩበት ሁኔታ ላይ መከሩ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ እና በኬንያ መካከል የአንድ አለቅ የድንበር ጣቢያዎችን ለማስፋፋት የሚያስችል ውይይት ተካሄደ፡፡
በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን እና የኬንያ ገቢዎች ባለስልጣን እንዲሁም የሀገራቱ ባለድርሻ ተቋማት የተሳተፉበት የአንድ አለቅ የድንበር አገልግሎት ጣቢያዎችን ለማስፋፋት እና በሌሎች የጉምሩክ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል ምክክር ተደርጓል፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የጉምሩክ አሥተዳደሮች ንግድን የማሳለጥ እና የድንበር ቁጥጥር ሥርዓትን የማጠናከር ቁልፍ ሚና አላቸው፡፡
የጉምሩክ ተቋማት ይህን ሚናቸውን ለመወጣት ከአቻ ተቋማት ጋር በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸው ማስገንዘባቸውን የኮሚሽኑ መረጃ አመላክቷል፡፡
ኮሚሽኑ ከኬንያ ገቢዎች ባለስልጣን ጋር በትብብር እየሠራ ያለበት ሁኔታም በይበልጥ መጠናከር እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
ከዓመታት በፊት አገልግሎት መስጠት የጀመረው በኢትዮጵያና በኬንያ ድንበር የሚገኘው የሞያሌ አንድ አለቅ የድንበር አገልግሎት ማዕከል፤ ተደጋጋሚ ፍተሻዎችን በማስቀረት የተፋጠነ የጉምሩክ አገልግሎት እንዲኖር ማስቻሉን አስረድተዋል፡፡
የአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ውህደት በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና እና በሌሎች አካባቢያዊ የኢኮኖሚ ብሎኮች አማካኝነት እየተፋጠነ መሆኑን ገልጸው፤ ኮሚሽኑ ኢትዮጵያ በዚህ ሂደት ውስጥ ግንባር ቀደም ሚናዋን እንድትወጣ የበኩሉን ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የኬንያ አምባሳደር ጆርጅ አሪና በበኩላቸው፤ በሀገራቱ ድንበር ላይ የአንድ አለቅ የድንበር አገልግሎት ማዕከል መገንባት የሁለቱን ሀገራት እድገት ለማፋጠን ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል፡፡
የዛው ውይይት ተጨማሪ የጋራ አንድ አለቅ የድንበር አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎችን ሱፍቱ እና ራሙ በሚባሉ የድንበር አካባቢዎች ለመገንባት ስለሚቻልበት ሁኔታ ብሎም በሀገራ መካከል የንግድ እና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስርን ለማጠናከር ያለመ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን እና የኬንያ ገቢዎች ባለስልጣን ትብብራቸውን ለማጠናከር የሚያስችል የትብብር የስምምነት ሰነድ ለመፈራረም የሰነድ ዝግጅት በአጭር ጊዜ እንዲጠናቀቅ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡