የጂኦሳይንስ ላቦራቶሪ ማዕከልን መልሶ ለማደራጀት የዲዛይንና የግንባታ ውል ስምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17 (ኤፍ ኤም ሲ) የጂኦ ሳይንስ መረጃን ለማመንጨት እና የማዕድናት ናሙና መመርመሪያ በመሆን የሚያገለግለውን የጂኦ ሳይንስ ላቦራቶሪ ማዕከልን መልሶ ለማደራጀት የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ፡፡
የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት እና የኢትዮጵያ ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ስምምነት፤ የማዕድን ሚኒስትር ሃብታሙ ተገኝ (ኢ/ር)፣ የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢጃራ ተስፋዬ እና የኢትዮጵያ ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ሽመልስ እሸቱ (ኢ/ር) ተገኝተዋል፡፡
ስምምነቱ የጂኦሳይንስ ላቦራቶሪ ማዕከል የበለጠ አገልግሎት እንዲሰጥ መልሶ ለማደራጀት ያለመ ሲሆን፤ ለዚህም ከ700 ሚሊየን ብር በላይ በጀት ከኢትዮጵያ ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር የፕሮጀክት ስምምነት ተፈርሟል፡፡
በስምምነቱ መሠረት ግንባታውን ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እንደሚሠራ መገለጹን የማዕድን ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
የጂኦሳይንስ ላቦራቶሪ ማዕከል የጂኦሳይንስ መረጃን በማመንጨትና ማዕድናትን በመመርመር ለረጅም ጊዜ እያገለገለ ይገኛል፡፡