የአድማ መከላከልና የመደበኛ ፖሊስ ምልምል ሰልጣኞች ሰላምን ለማጽናት በሚያስችል ቁመና ላይ መሆናቸው ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአማራ ክልል የአድማ መከላከልና የመደበኛ ፖሊስ ምልምል ሰልጣኞች ከክልሉ አልፎ የሀገርን ደኅንነት ለመጠበቅ የሚያስችል ዝግጁነት ላይ እንደሚገኙ የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ደሳለኝ ጣሰው ገለጹ
ኃላፊው በብር ሸለቆ መሠረታዊ የውትድርና ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ተገኝተው ምልምል ሠልጣኞችን በማበረታታት የሥልጠናውን ዓላማ በተመለከተም ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ሠልጣኞች የክልሉን ሰላም በዘላቂነት በማረጋገጥ ሕዝቡ ከገባበት ፈተና ተላቆ ፊቱን ወደ ልማት እንዲያዞር በማድረግ ረገድ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡
የስልጠናው ዋና ዓላማ ነጻ፣ ገለልተኛ፣ ወታደራዊ ሥነ ምግባር የተላበሰ እንዲሁም በሥነ ልቦና ያደገና በራስ አቅም የክልሉን ሰላም ማረጋገጥ የሚችሉ ሠልጣኞችን ማፍራት እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ኃላፊው አክለውም፥ ሠልጣኞቹ ከክልል አልፎ የሀገርን ደኅንነት ለመጠበቅ የሚያስችል ቁመና እና ዝግጁነት ላይ መኾናቸውን አረጋግጠናል ብለዋል።
ሠልጣኞቹ በአመለካከት፣ በንድፈ ሃሳብና በተግባር የታገዘ ሥልጠና መውሰዳቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡