ኢትዮ ቴሌኮም እና ማስተር ካርድ የዲጂታል የፋይናንስ አገልግሎቶችን በጋራ ለማሻሻል ያለመ ውይይት አደረጉ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬሕይዎት ታምሩ እና የማስተርካርድ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ማርክ ኤሊዮት አዳዲስ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን ለማስጀመር የትብብር እድሎችን ለመፈተሽ የሚያስችል ውይይት አድርገዋል፡፡
ይህ የትብብር ማእቀፍ የቴሌብርን እና የማስተርካርድ ፕላትፎርሞችን በመጠቀም የዲጂታል ፋይናንስ ሶሉሽኖችን ለማሳደግ፣ የፋይናንስ ተደራሽነትን በከፍተኛ ሁኔታ ለማስፋት እና ዘላቂ እድገትን ለማበረታታት ያለመ ነው ተብሏል።
ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ በዚሁ ወቅት፤ ተቋማቸው በአፍሪካ ትልቅ የደንበኞች ቁጥር እና ግዙፍ መሠረተ ልማት ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ይህም አዳዲስ እድሎችን ለመክፈት የሚያስችል አስቻይ ሁኔታ እንደፈጠረለት ጠቅሰው፤ በአጋርነት ለመስራት ያላቸውን ተነሳሽነት አረጋግጠዋል።
ማርክ ኤሊዮት በበኩላቸው፤ የኢትዮ ቴሌኮም ፈጣን የደንበኞች ቁጥር ዕድገት እና ግዙፍ የመሰረተ ልማት አቅም ለአጋርነት ተመራጭ እንደሚያደርገው አረጋግጠዋል፡፡
ለማስተርካርድ ይህ ትብብር መልካም አጋጣሚ የፈጠረለት መሆኑን እና ለተግባራዊነቱ ያላቸውን የላቀ ቁርጠኝነት ገልጸዋል፡፡
ይህ ስትራቴጂያዊ ትብብር ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ ያላትን ተወዳዳሪነት በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳድግ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ዘላቂ ዕድገትንና የሀብት ፈጠራን በማበረታታት አካታች እና ሁሉን አቀፍ የዲጂታል ፋይናንስ ምህዳር እንዲሁም ዘላቂ እድገት ለማስመዝገብ የሚያስችል መሆኑም ነው የተመለከተው፡፡