ኮፕ 30 የተገቡ ቃሎች ወደ ተግባር የሚቀየሩበት እንዲሆን ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በብራዚል የሚካሄደው 30ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ የተገቡ ቃሎች ወደ ተግባር የሚቀየሩበት ሊሆን እንደሚገባ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ።
የ2025 የፒተርስበርግ የአየር ንብረት ለውጥ ምክክር በጀርመን በርሊን ከተማ እየተካሄደ ነው።
በውይይቱ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) እንደገለጹት÷ ኢትዮጵያ የፓሪስ የአየር ንብረት ለውጥ ግቦችን ለመተግበር በቁርጠኝነት ትሰራለች።
በአሳሳቢ ሁኔታ እየጨመረ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ ለመግታት የጋራ ቁርጠኝነት በማደስ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ በቀጣዩ መስከረም ወር የሚካሄደውን 2ኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔን እንደምታሰናዳ በመግለጽ ለአየር ንብረት ለውጥ ርምጃዎች ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በብራዚል የሚካሄደው 30ኛው በተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ የተገቡ ቃሎች ወደ ተግባር በመቀየር በትክክለኛው ጎዳና ለመጓዝ ወሳኝ የሽግግር ነጥብ እንዲሆን ጥሪ ታቀርባለች ብለዋል።
ሚኒስትሯ ከጉባዔው ጎን ለጎን ከኮፕ 30 ፕሬዚዳንት አንድሬ ኮሪያ ዶ ላጎ እና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ማዕቀፍ (ዩኤንኤፍሲሲ) ዋና ፀሐፊ ሳይመን ስቲል ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱ ለዋና ጸሐፊው እና ለፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያ በምታዘጋጀው አህጉራዊ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ላይ እንዲሳተፉ ጋብዘዋል።
በበርሊን ከተማ እየተካሄደ የሚገኘው የ2025 የፒተርስበርግ የአየር ንብረት ለውጥ ምክክር በነገው ዕለት ቀጥሎ እንደሚካሄድ የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።