Fana: At a Speed of Life!

የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስና በውጭ ምንዛሪ ተመን ላይ የሚታዩ ግምታዊ አስተሳሰቦችን ለመቆጣጠር የባንኩ የፖሊሲ ተመን 15 በመቶ ሆኖ እንዲቆይ ተወሰነ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የዋጋ ግሽበትን ለመቀነስና በውጭ ምንዛሪ ተመን ላይ የሚታዩ ግምታዊ አስተሳሰቦችን ለመቆጣጠር የባንኩ የፖሊሲ ተመን 15 በመቶ ሆኖ እንዲቆይ እና በባንኮች የብድር ዕድገት ላይ የተቀመጠው የወለድ ተመን 18 በመቶ ገደብ እንዲቀጥል መወሰኑን የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ሁለተኛ ስብሰባውን መጋቢት 16 ቀን 2017 ዓ.ም አካሂዷል፡፡

ከሚቴው በስብሰባው የማክሮ ኢኮኖሚ ግምገማዎችና የቅርብ ጊዜ የወደፊት እይታዎች በመነሣት በገንዘብ ፖሊሲው ተግባራዊ የሚደረጉ የፖሊሲ ምክረ-ሐሳቦችን ለቦርድ አቅርቦ አስወስኗል፡፡

የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ስብሰባ ቁጥር ሁለት ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ሁለተኛ ስብሰባውን መጋቢት 16 ቀን 2017 አካሂዷል፡፡

በተሻሻለው የባንኩ የማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1359/2025፣ አንቀጽ 23፣ በተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት መሠረት የተቋቋመው የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ከባንኩ ዋጋን ከማረጋጋትና የኢኮኖሚ ዕድገትን ከመደገፍ ቀዳሚ ዓላማ ጋር የተጣጣሙ የገንዘብ ፖሊሲ ምክረ ሐሳቦችን ለባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ በማቅረብ ያስጸድቃል፡፡

በዚህ ረገድ፣ ኮሚቴው የኢትዮጵያን የዋጋ ግሽበት፣ የፊስካል፣ የውጭ ኢኮኖሚ፣ የገንዘብ አቅርቦትና የፋይናንስ ዘርፍ እንቅስቃሴዎችን፣ እንዲሁም በሀገር ውስጥ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታዎች ላይ ጉልህ አንደምታ ያላቸው ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችን ይገመግማል፡፡

ኮሚቴው ከእነዚህ የማክሮ ኢኮኖሚ ግምገማዎችና የቅርብ ጊዜ የወደፊት እይታዎች በመነሣት በገንዘብ ፖሊሲው ተግባራዊ የሚደረጉ የፖሊሲ ምክረ-ሐሳቦችን ያቀርባል፡፡

በዚሁ መሠረት፤ ኮሚቴው የገመገማቸው ዐበይት ጉዳዮች የሚከተሉት ናቸው፡-

የዋጋ ግሽበት፡- ካለፈው የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ስብሰባ ወዲህ፣ ዓመታዊ የዋጋ ግሽበት እየቀነሰ በመምጣት የካቲት ወር 2017 መጨረሻ 15.0 በመቶ መድረሱን ኮሚቴው ተገንዝቧል፡፡ ባለፉት ጥቂት ወራት የዋጋ ግሽበት በተከታታይ እየረገበ የመጣው ብሔራዊ ባንክ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ በመከተሉ፣ የግብርና ምርት በመሻሻሉና በአስተዳደራዊ ዋጋዎች ላይ እየተወሰደ ያለው ማሻሻያ ቀስ በቀስ በመተግበሩ ምክንያት እንደሆነ ይገመታል፡፡

ምግብ-ነክ የዋጋ ግሽበት በየካቲት ወር 2017 መጨረሻ 14.6 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው 3 በመቶ ጋር ሲነጻጸር በእጅጉ ያነሰ ነው፡፡ በተመሳሳይ፣ ምግብ-ነክ ያልሆነ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ቀንሶ 15.6 በመቶ የደረሰ ቢሆንም ባለፉት ጥቂት ወራት የማንሰራራት አዝማሚያ አሳይቷል፡፡

በየካቲት ወር 2017 ላይ የ0.5 በመቶ ወርሃዊ ዕድገት የታየ ሲሆን፣ ይህም ለአራት ተከታታይ ወራት የተከሰተ ዝቅተኛ ዕድገት እንደሆነና የዋጋ ግሽበት በኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው አዲሰ ተጽእኖ ዝቅተኛ መሆኑን ያመላክታል፡፡

ዕድገትና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ፡- የሀገር ውስጥ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አመላካቾች የተጠናከረ የዕድገት አዝማሚያ መኖሩን እንደሚያሳዩ ኮሚቴው ተገንዝቧል፡፡ በአብዛኞቹ የሀገሪቱ አካባቢዎች የታየው ምቹ የመህር ዝናብ ወራትና በግብርናው ዘርፍ እየተወሰዱ ያሉ የአቅርቦት ማሻሻያ ውጥኖች በዘንድሮው ዓመት ከፍተኛ የሰብል ምርት እንደሚኖር ያሳያሉ፡፡ በሌሎች ዘርፎችም፣ በተለይም በኢንዱስትሪ፣ በሸቀጦች ወጪ ንግድ (በተለይም በቡናና በወርቅ)፣ እንዲሁም በአገልግሎት ወጪ ንግድ (በተለይም በአየር ትራንስፖርትና በቱሪዝም) ዘርፎች የተጠናከረ ዕድገት እንደሚኖር ይገመታል፡፡

የገንዘብ ሁኔታ፡- ካለፈው የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ስብሰባ ወዲህ የገንዘብ ዝውውር እድገት መጠነኛ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው የብድር፣ የፊስካልና የውጭ ኢኮኖሚ ሁኔታዎች ላላ በመደረጋቸው ነው፡፡እስከ ጥር ወር 2017 ድረስ በኢኮኖሚ ውስጥ የሚዘዋወረው የጠቅላላ ገንዘብ አቅርቦት (broad money supply) የ22.8 በመቶ፣ መሠረታዊ ገንዘብ (base money) 42.0 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት ሲያሳዩ፣ የሀገር ውስጥ ብድር በ19.8 በመቶ ጨምሯል፡፡ መሠረታዊ ገንዘብ ፈጣን ዕድገት ሊያሳይ የቻለው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከወርቅ ሽያጭ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ክምችት በመያዙና ተመጣጣኝ የሀገር ውስጥ ገንዘብ ወደ ባንክ ስርዓት እንዲገባ በመደረጉ ነው፡፡

የወለድ ተመን ሁኔታ፡- በገበያ ላይ የተመሠረቱ የአጭር ጊዜ የወለድ ተመኖች ለመጀመሪያ ጊዜ ከዋጋ ግሽበት በላይ መሆናቸውን ኮሚቴው ተገንዝቧል፡፡ ለምሳሌ፤ የ364 ቀን የመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነድ የወለድ ተመን አምና ታህሳስ ወር መጨረሺያ ላይ ከነበረበት 15.9 በመቶ ዘንድሮ የካቲት ወር 2017 መጨረሻ 17.7 በመቶ ደርሷል፡፡

ባንኮች እርስ በርሳቸው በሚበዳደሩበት ገበያ አማካይ የወለድ ተመን የካቲት ወር ላይ 16.7 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ብሔራዊ ባንክ ባስቀመጠው የ15 በመቶ የወለድ ተመን ክልል( በ3 በመቶ ያነሰ ወይም ከፍ ያለ) ውስጥ ይገኛል፡፡ በባንኮች መካከል እየተደረገ ያለው የገንዘብ ግብይት መጠን በፈጣን ሁኔታ ማደጉን ቀጥሎ በየካቲት ወር 2017 መጨረሻ ብር 338.8 ቢሊዮን ደርሷል፡፡

የባንክና የፋይናንስ ዘርፍ መረጋጋት፡- የባንክ ዘርፍ ዝቅተኛ የተበላሸ ብድር እና በቂ ካፒታል ያለው በመሆኑ ጤናማና የተረጋጋ እንደሆነ ኮሚቴው ገምግሟል፡፡ ይሁን እንጂ፣ አንዳንድ ባንኮች በተወሰነ መልኩ የጥሬ ገንዘብ አከል (liquidity) እጥረት ይታይባቸዋል፡፡ ይህም የሆነው በተወሰኑ ባንኮች ዘንድ የብድርና የተቀማጭ ሂሳብ (oan to deposit ratio) ጥምርታ ከፍተኛ በመሆኑ ነው፡፡ ነገር ግን ፣ የባንክ ለባንክ የገንዘብ ግብይት (nterbank Money Market) እና በብሔራዊ ባንክ በኩል ቋሚ የብድር አገልግሎት መጀመራቸው የአንዳንድ ባንኮች ችግር እየተቀረፈ ይገኛል፡፡

የፊስካል ሁኔታ፡- ጥንቃቄ የተሞላበት የፊስካል ፖሊሲ ሥርዓት መተግበሩን ቀጥሏል፡፡ ጥብቅ የፊስካል ዲሲፕሊን መኖሩ በዘንድሮው በጀት ዓመት ለበጀት ጉድለት ማሟያ ከብሔራዊ ባንክ ብድር እንዳይወሰድ የረዳና ለማዕከላዊ ባንኩ የገንዘብ ፖሊሲ አቋም ከፍተኛ ድጋፍ የሚሰጥ ክስተት ሆኗል፡፡

የውጭ ኢኮኖሚ ዘርፍ፡- የውጭ ኢኮኖሚ ዘርፍ እንቅስቃሴ ትልቅ መሻሻል እንዳሳየ ኮሚቴው ተገንዝቧል፡፡ በመሆኑም፣ ባለፈው ሐምሌ ወር 2016 በተደረገው የውጭ ምንዛሪ ተመን ማሻሻያ ምክንያት የሸቀጦችና የአገልግሎቶች ወጪ ንግድና ሐዋላ፣ እንዲሁም የካፒታል ሂሳብ ከፍተኛ ዕድገት በማሳየታቸው የከረንት አካውንት በመጀመሪያው የበጀት ግማሽ ዓመት ትርፍ አሳይቷል፤ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችትም እንዲጨምር አድርጓል፡፡

ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች፡- ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገት እ.ኤ.አ በ 2025 እና በ 2026 ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና 3.3 በመቶ ዕድገት እንደሚያሳይ የዓለም የገንዘብ ድርጅት የጥር ወር መረጃ ያመላክታል፡፡ በአንጻሩ፣ ዓለም አቀፍ የዋጋ ግሽበት እ.ኤ.አ በ2025 ወደ 4.2 በመቶ እንዲሁም እ.ኤ.አ በ2026 ደግሞ ወደ 3.5 በመቶ ዝቅ እንደሚል ተተንብዮአል፡፡ ይሁን እንጂ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚንጸባረቁ የጂኦ ፖለቲካ እንቅስቃሴዎችና አለመረጋጋቶች በዓለም አቀፍ የታሪፍና የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ በሚያሳድሩት ተጽእኖ የዋጋ ግሽበት ሊባባስ ይችላል፡፡

አሁን ያለው የዓለም የሸቀጦች ዋጋ በጥቅሉ ለሀገራችን ምቹ ነው ሊባል ይችላል፡፡ ለምሳሌ፣ የነዳጅ ዋጋ የበጀት ዓመቱ ከተጀመረ ወዲህ 9 በመቶ ሲቀንስ ፣ በአንጻሩ፣ የዋና ዋና የወጪ ምርቶች ዋጋ (የቡናና የወርቅ) ከመቼውም ጊዜ በላይ በከፍተኛ ደረጃ በመጨመሩ ለውጭ ክፍያ ሚዛን መሻሻል አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ግምገማና ውሳኔ

ምንም እንኳን የቅርብ ጊዜ የዋጋ ግሽበት ሁኔታ አበረታችና የመርገብ አዝማሚያ ቢያሳይም፣ አሁንም ቢሆን የዋጋ ግሽበቱ ከፍተኛና በመካከለኛ ጊዜ ሊደረስበት ከታሰበው የነጠላ አሃዝ ግብ በላይ በመሆኑ አሁንም ቢሆን ጠበቅ ያለ የገንዘብ ፖሊሲ መጠቀም አስፈላጊ እንደሆነ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴው ተገንዝቧል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም የዋጋ ግሽበቱን ትርጉም ባለው መልኩ ለመቀነስ በሙሉ ቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል፡፡ በመሆኑም የዋጋ ግሽበቱ በቀጣይ ባሉት ወራቶች ቅናሽ እንዲያሳይ ጥንቃቄ የተሞላበት አካሄድ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ኮሚቴው በአጽንኦት ያምናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ በኮሚቴው አመለካከት፣ ጠንቃቃ የገንዘብ ፖሊሲ መከተልን አስፈላጊ የሚያደርጉ ማክሮ ገጽታዎች አሉ፡፡ ኮሚቴው እነዚህን ሁኔታዎች በማመዛዘን አሁን ያለውን ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ማስቀጠል እንደሚገባ አስተውሏል፡፡

የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ግምገማና የውሳኔ ሐሳብ

እስካሁን የታየው የዋጋ ግሽበትን የመቀነስ ጥረት አበረታች ቢሆንም፣ የዋጋ ግሽበት አሁንም ቢሆን ከተጠበቀው በላይና በመካከለኛው ጊዜ ከሚደረስበት ከነጠላ አሃዝ ግብ ከፍ ያለ መሆኑን ኮሚቴው ተረድቷል፡፡

በመሆኑም የዋጋ ግሽበት ትርጉም ባለው መልኩ እስኪቀንስ ድረስ አሁን ያለው የገንዘብ ፖሊሲ አቋም ተገቢ በመሆኑ ሊቀጥል እንደሚገባ ኮሚቴው ተስማምቷል፡፡ እንዲሁም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚታየው የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሊሰጠውና ወደ ኢኮኖሚው የሚገባው የገንዘብ መጠን በገንዘብ ፖሊሰው ላይ ያልተፈለገ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳያሳድር መጠንቀቅ እንደሚያሻ ኮሚቴው አምኖበታል፡፡

ከእነዚህ ግምቶች በመነሣት ኮሚቴው የሚከተሉትን የገንዘብ ፖሊሲ ምክረ ሐሳቦች ለቦርድ አቅርቦ አስወስኗል፡፡

1. አሁንም ቢሆን ከፍ ብሎ የሚታየውን የዋጋ ግሽበት ለመቀነስና በውጭ ምንዛሪ ተመን ረገድ የሚታዩ ግምታዊ አስተሳሰቦችን (expectations) ለመቆጣጠር ሲባል የብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ተመን (National Bank Rate) አሁን ባለበት 15 በመቶ እንዲቆይ፤

2. በወለድ ተመን ላይ ወደ ተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ አስተዳደር ሥርዓት የሚደረገው ሽግግር ገና በመሆኑ፣ በባንኮች የብድር ዕድገት ላይ የተቀመጠው 18 በመቶ ገደብ እንዲቀጥል፤

3. በአሁኑ ወቅት ብሔራዊ ባንክ ለሚሰጣቸው ቋሚ የተቀማጭ ሂሳብ አገልግሎት (standing deposit facility)፣ ለቋሚ የብድር አገልግሎት (standing lending facility) የሚከፈሉ የወለድ ተመኖች ባሉበት እንዲቀጥሉ፣ እንዲሁም ባንኮች በብሔራዊ ባንክ የሚያስቀምጡት የግዴታ መጠባበቂያ ተቀማጭ ሂሳብ በነበረበት እንዲቆይ ተወስኗል፡፡

የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴው ቀጣይ የገንዘብ ፖሊሲ ውሳኔዎች በቀጣይ ወራት በሚከሰቱ የዋጋ ግሽበት ውጤቶች ግምገማ ላይ የተመሠረቱ እንደሚሆኑ ግንዛቤ ተወስዷል፡፡ ቀጣዩ የኮሚቴው ስብሰባ ሰኔ ወር 2017 መጨረሻ ላይ እንዲሆን ተወስኗል፡፡

የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ
መጋቢት 16 ቀን 2017

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.