ፔፕ ጋርዲዮላ በማንቼስተር ሲቲ…
ማንቼስተር ዩናይትድን በታሪክ ማማ ላይ የሰቀሉት ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ፔፕ ጋርዲዮላ በፈረንጆቹ 2016 ወደ ማንቼስተር ሲቲ ሲመጣ ስለ ስፔናዊው አሰልጣኝ ተጠይቀው የሰጡት መልስ “ይህ ቡንደስ ሊጋ ወይም ስፔን ላሊጋ ሳይሆን የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ነው” የሚል ነበር፡፡ ይህ ምላሻቸውም ፔፕ በሁለቱ ሊጎች ያገኘውን ድል በፕሪሚየር ሊጉ መድገም አይችልም ለማለት እንደነበረ ግልጽ ነው፡፡
ፈርጉሰን ‘ጩኸታም ጎረቤቶች’ ብለው የሚጠሯቸው ሲቲዎች ‘እኔ በህይወት እያለሁ ከዩናይትድ በላይ ሆነው ድልን ሲጎናጸፉ ማየት አልፈልግም’ የሚል አቋምም ነበራቸው፡፡
ጋርዲዮላ የባርሴሎና አሰልጣኝ በነበረበት ወቅት ፈርጉሰን ከሚመሩት ማንቼስተር ዩናይትድ ጋር ተገናኝተው በበላይነት ማጠናቀቅ ችሎ ነበር፡፡
ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ከማንቼስተር ዩናይትድ ጋር ከተለያዩ ከሶስት አመት በኋላ ፔፕ ጋርዲዮላ ማንቼስተር ሲቲን ተረከበ፡፡
ፔፕ ሊጉን በተቀላቀለበት የውድድር አመት ሲቲን በፕሪሚየር ሊጉ 3ኛ ደረጃን ይዞ እንዲያጠናቅቅ ማድረግ ችሏል።
ፔፕ በስፔን ቆይታው የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግን ጨምሮ ትላልቅ ዋንጫዎችን ከፍ በማድረግ ባርሴሎናን በስፔን ምድር ላይ የካታሎናውያን ኩራት አድርጎታል፡፡
ከዛም ወደ ጀርመን በማቅናት ከባየርን ሙኒክ ጋር የቡንደስ ሊጋውን ዋንጫ ለሶስት ተከታታይ አመታት ማሸነፍ ችሏል፡፡
አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ባለፉት ዓመታት ከማንቼስተር ሲቲ ጋር የማይቻለውን እንዲቻል አድርጓል፡፡
ጎረቤቶቻቸው ማንቼስተር ዩናይትዶች ‘በአንድ የውድድር አመት የሶስትዮሽ ዋንጫ ከእኛ ውጭ ያሸነፈ የለም፤ ከዚህ በኋላም የሚያሸንፍ የለም እያሉ የሚኩራሩበትን የታሪክ ሪከርድ’ ፔፕ ሲቲን እየመራ በ2022/23 የውድድር አመት መጋራት ችሏል፡፡
ሲቲዎች ይህም አልበቃ ብሏቸው የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ለተከታታይ አራት አመታት በማሳካት ታሪክን መጋራት ሳይሆን በፕሪሚየር ሊጉ ታሪክ ብቸኛ ሆነው ተቀምጠዋል፡፡
ይህ በማን ሆነ ካላችሁ.. በስፔናዊው አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ነው፡፡ ዘ ሲቲዝንስ በመባል የሚታወቁት ሲቲዎች ፔፕ ጋርዲዮላ ከመምጣቱ በፊት በሮቤርቶ ማንቺኒና በፔሌግሪኒ እየተመሩ የሊጉን ዋንጫ ማሳካታቸው ይታወሳል፡፡
ባለፉት ሰባት የውድድር አመታት ስድስት የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫዎችን አሳክተዋል፡፡
ብዙዎች የፔፕ ጋርዲዮላ ስኬት ከረብጣ ገንዘብ ጋር ሲያይዙ ይደመጣሉ።
ይህንን መከራከሪያ የማይቀበሉ ሌሎች ወገኖች ደግሞ ባለፉት አራትና አምስት አመታት ቼልሲ እና ማንችስተር ዩናይትድ ቢሊየን ፓውንድ ቢያወጡም ከስኬት ጋር ግን መገናኘት እንዳልቻሉ በመግለጽ በገንዘብ ብቻ የተገኘ ስኬት እንዳልሆነ ይሞግታሉ፡፡
የፔፕ ቡድን የጠንካራ ቡድኖችን ትንሿን ድክመት ትልቅ ድክመት አድርጎ አጉልቶ በማውጣት የሚሰተካከለው የለም፡፡
ማንቼስተር ሲቲዎች በፔፕ ጋርዲዮላ እየተመሩ በርካታ ታሪኮችን በወርቅ ቀለም ፅፈዋል …፤ ተቃናቃኞቻቸውን በሰፊ የጎል ልዩነት ረትተዋል…፤ በዋንጫ ተንበሽብሸዋል፡፡ ጋርዲዮላ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ሲመጣ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን የሰጡት አስተያየት ስህተት መሆኑን በስራቸው አሳይተዋል፡፡
ፈርጉሰንም የማንቼስተር ሲቲን ስኬት ሳይወዱ በግዳቸው በአይናቸው ተመልክተዋል።
ባለፈው ክረምት ከሊቨርፑል ጋር የተለያዩት አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ ‘ፔፕ በአለማችን ላይ ካሉ አሰልጣኞች ሁሉ የመጀመሪያው ነው’ በማለት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ፔፕ በማንቼስተር ከተማ በውሃ ሰማያዊ ቀለም የማይናወጥ የእግር ኳስ ታሪክ ፅፏል፡፡
አርሰናል፣ ሊቨርፑል እና ሌሎች የሊጉ ክለቦች የፔፕ ጋርዲዮላን ቡድን ለማፈራረስ ብዙ ቢጥሩም ማንቼስተር ሲቲን የማይቀመስና እንደ እሳት ከሩቅ የሚያቃጥል ቡድን ማድረግ ችለዋል።
ነገር ግን ባለፉት ዓመታት ለሁሉም ክለቦች ፈታኝና አልቀመስ ብሎ የቆየው በአሰልጣኝ ፔፕ ጋዲዮላ የሚመራው ማንቼስተር ሲቲ በዚህ የውድድር ዓመት ላለፉት ዓመታት በነበረበት ከፍታው መዝለቅ አልቻለም።
በተከታታይ አራት ዓመታት የሊጉን ዋንጫ ማሳካት የቻለው ማንቼስተር ሲቲ በዚህ የውድድር ዓመት ከዋንጫ ፉክክሩ ርቆ በሊጉ እስከ 4ኛ ያለውን ደረጃ ይዞ ለማጠናቀቅ እየተፎካከረ ይገኛል፡፡
የ2024/25 የውድድር ዘመን ከመጀመሩ አስቀድሞ ምናልባትም ማንቼስተር ሲቲ በጋርዲዮላ እየተመራ ለተከታታይ አምስተኛ ጊዜ የሊጉን ዋንጫ ሊያነሳ ይችላል የሚሉ ግምቶች ነበሩ፤ ነገር ግን ግምቶቹ ሁሉ ሳይሰምሩ ቀርተው በጣም የተቸገረውንና በታሪኩ አይቶት የማያውቀው ሽንፈቶችን ለማስተናገድ ተገዷል፡፡
በውድድር ዓመቱ በተከታታይ ጨዋታዎች ቡድኑ ውጤት ማጣቱን ተከትሎ ፔፕ ጋዲዮላ አፍንጫቸውን በገዛ እጃቸው ሞነጫጭረው እስከ ማድማት ደርሰዋል፡፡
በዚህ የውድድር ዓመት ሳይጠበቅ ከሁሉም ነገር ገና በጊዜ ውጭ የሆነው ማንቼስተር ሲቲ በሚቀጥለው የውድድር ዘመን በርካታ ታሪኮችን በክለቡ ከሰራው አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ጋር በቀደመ ብቃቱ ይመለስ ይሆን የሚለው ይጠበቃል፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ