በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተከሰተውን የዳልጋ ከብቶች በሽታ መቆጣጠር ተቻለ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ተከስቶ የነበረውን የዳልጋ ከብቶች በሽታ መቆጣጠር እንደተቻለ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊና የእንስሳት ጤናና ግብዓት አቅርቦት ዘርፍ ኃላፊ ዶ/ር አዲሱ ኢዮብ በሽታውን ለመቆጣጠር የባለሙያዎች ቡድን ተቋቁሞ እስከ ቀበሌ ድረስ እየሠራ መቆየቱን ለፋና ዲጂታል ገልጸዋል።
በሽታውን ለመቆጣጠር የተደረገው ርብርብ ውጤት ማምጣቱን ጠቅሰው፤ የበሽታው ምልክት ከታየበት ከመጋቢት 5 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በተሰራው ሥራ 4 ሺህ 453 የዳልጋ ከብቶች ህክምና እንደተደረገላቸው ተናግረዋል።
በሽታው ወደ ሌሎች ከብቶች እንዳይሰራጭ 150 ሺህ ለሚሆኑ የዳልጋ ከብቶች ክትባት እንደተሰጠ ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅት ተመሳሳይ በሽታ እንዳይከሰትና እንዳይሰራጭ በሁሉም የክልሉ ዞኖች ክትባት የመስጠት ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸው÷ ለ1 ሚሊየን የዳልጋ ከብቶች ክትባቱን ለማድረስ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
በሽታው በክልሉ ጋሞ፣ ጎፋ እና ደቡብ ኦሞ ዞኖች ውስጥ በሚገኙ ሰባት ወረዳዎች ላይ መከሰቱን ያስታወሱት ዶ/ር አዲሱ÷ በበሽታው የሞቱ ከብቶች መኖራቸውንና የማጣራት ሥራ አለመጠናቀቁን አብራርተዋል።
በክልሉ ለእንስሳቱ ክትባት ለመስጠት የሚያስችል ዓቅም በመኖሩ ሕብረተሰቡ እንስሳቶችን እንዲያስከትብ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በአድማሱ አራጋው