የኮይሻ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ የሕዝቦችን ኢኮኖሚያዊ ችግር በሚፈታ መልኩ እየተገነባ ነው
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኮይሻ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ፕሮጀክት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ሕዝቦችን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በሚፈታ መልኩ እየተገነባ መሆኑ ተገለጸ፡፡
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥ ሥራ ኃላፊዎች የኮይሻ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ፕሮጀክትን ጎብኝተዋል፡፡
በዚሁ ወቅት የፕሮጀክቱ ግንባታ 65 በመቶ መድረሱ የተገለጸ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
በ2 ነጥብ 5 ቢሊየን ዩሮ ወጪ እየተገነባ የሚገኘው ይህ ፕሮጀክት፤ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በኮንታ ዞን ኮንታ ኮይሻ ወረዳ እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን መሎ ኮዛ ወረዳ መካከል ላይ ይገኛል።
ፕሮጀክቱ የሁለት ክልሎች ሕዝቦችን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በሚፈታ መልኩ እየተገነባ እንደሚገኝም ነው የተገለጸው፡፡
በተጨማሪም ፕሮጀክቱ የአካባቢው ተፈጥሮ በይበልጥ ተጠብቆ የሚለማበትና ለጎብኚ መስኅብ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚያበረክት መገለጹን የጎፋ ዞን ኮሙኒኬሽን መምሪያ መረጃ አመላክቷል፡፡