Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ እና አልጀሪያ በኢነርጂ ዘርፍ በትብብር መሥራት እንደሚፈልጉ ገለጹ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የአልጀሪያ ኢነርጂ፣ ማዕድንና ታዳሽ ኢነርጂ ሚኒስትር መሐመድ አርካብ ጋር ተወያዩ፡፡

በውይይታቸውም ኢትዮጵያና አልጀሪያ በቀጣናዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ በትብብር እየሠሩ መሆኑን ሚኒስትር ሐብታሙ (ዶ/ር ኢ/ር) አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በምሥራቅ አፍሪካ የኃይል ትሥሥር እንዲፈጠር በማድረግ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተች መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በዚህም ኢነርጂ ላይ የሚሠሩ የአልጀሪያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የኃይል ልማት ዘርፍ ላይ መሳተፍ የሚችሉበት የኢንቨስትመንት ዕድል መኖሩን አስገንዝበዋል፡፡

ለዚህም በኢትዮጵያ በኢነርጂ ዘርፍ የሚወጡ ዓለም አቀፍ ጨረታዎች ላይ የአልጀሪያ ድርጅቶች እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሚኒስትር መሐመድ በበኩላቸው፤ በኃይል ማምረት እና ሥርጭት እንዲሁም ለኃይል ስርጭት አስፈላጊ የሆነ ግብዓት የሚያመርቱ የአልጀሪያ  ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መሰማራት እንደሚፈልጉ አረጋግጠዋል፡፡

በኢነርጂ አቅም ግንባታ ዘርፍ ኢትዮጵያውያን የኢነርጂ ባለሙያዎች በአልጀሪያ አቅማቸውን የሚገነቡበት ዕድል ይመቻቻል ማለታቸውን የውኃና ኢነርጂ ሚስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

በተመሳሳይ የማዕድን ሚኒስትር ሐብታሙ ተገኝ (ኢ/ር) በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ ከአልጄሪያ የኢነርጂ፣ ማዕድንና ታዳሽ ኃይል ሚኒስትር መሐመድ አርካብ እና ልዑካቸው ጋር ተወያይተዋል፡፡

በዚሁ ወቅትም ሀገራቱ በማዕድን ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

ከውይይታቸው በኋላም የአልጀሪያ ልዑክ የማዕድን ጋለሪን መጎብኘቱን የማዕድን ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.