Fana: At a Speed of Life!

 ኢትዮጵያ በዓለም ንግድ ድርጅት ስብሰባ ከ19 ሀገራትና ከዓለም ባንክ ድጋፍ ማግኘቷ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በ5ኛው የዓለም ንግድ ድርጅት ስብሰባ ከ19 ሀገራትና ከዓለም ባንክ ድጋፍ ማግኘቷን የንግድ እና ቀጣናዊ ትሥስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ በ5ኛው የዓለም ንግድ ድርጅት ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ ያከናወነቻቸውን ተግባራት አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም፤ ኢትዮጵያ በስብሰባው ላይ የነበራት ተሳትፎ የተሳካ ነበር፤ ከ19 ሀገራት እና ከዓለም ባንክም ድጋፍ አግኝታለች ብለዋል፡፡

በድርድር ሒደቱ ብዙ ተስፋ ሰጭ ነገሮች መገኘታቸውን ያነሱት ሚኒስትሩ፤ ስድስተኛው እና ሰባተኛው የስራ ላይ ቡድን ስብሰባ የፊታችን ሐምሌ እና ሕዳር ወር ላይ እንደሚካሄድ ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ያሳካቻቸው ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚክ ማሻሻያዎች በዓለም ንግድ ድርጅት በኩል በበጎ ጎን መታየቱንም አንስተዋል፡፡

በዚህም መሰረት በፈረንጆቹ 2026 በካሜሮን በሚካሄደው የዓለም ንግድ ድርጅት ጉባዔ ላይ ኢትዮጵያ አባል እንደምትሆን ይጠበቃል ነው ያሉት፡፡

ኢትዮጵያ ለድርጅቱ የአባልነት ጥያቄ ካቀረበች 23 ዓመታት እንደሆናትም ተናግረዋል፡፡

ድርጅቱ ከተመሰረተ 30 ዓመታት ያስቆጠረ እንደሆነና 166 ሀገራት አባል መሆናቸውን ገልጸው፤ ከእነዚህ መካከል 38 ያህሉ በድርድር የተቀላቀሉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያን ጨምሮ 22 ሀገራት ለድርጅቱ የአባልነት ጥያቄ አቅርበው ይሁንታን በመጠበቅ ላይ እንደሚገኙም ነው ያመላከቱት፡፡

በፀጋዬ ንጉሥ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.