Fana: At a Speed of Life!

በጸጥታ ችግር ምክንያት ከ7 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ አልተመለሱም

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠረ የጸጥታ ችግር ምክንያት ከ7 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው አለመመለሳቸውን የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ገለጹ፡፡

ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) እና የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች እና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በባሕር ዳር ከተማ የክልሉ የትምህርት ንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ ነው።

ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠረ የጸጥታ ችግር ምክንያት ከ7 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዳልተመለሱ ገልጸዋል።

ግጭቶች የሕጻናትና ወጣቶችን አዕምሮ በመመረዝ የወደፊት ዕድላቸውን የሚያሰናክሉ በመሆናቸው፤ በአስቸኳይ መፍትሔ ሊሰጣቸው እንደሚገባ በአጽንኦት አንስተዋል፡፡

ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ በበኩላቸው፥ በክልሉ በትምህርት ላይ የደረሰውን የከፋ ጉዳት በመቀልበስ ወደነበረበት የመማር ማስተማር ሁኔታ ለመመለስ ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በክልሉ በጸጥታ ችግር ምክንያት በዘንድሮው የትምህርት ዘመን 7 ሚሊየን ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር ቢታቀድም፤ የተመዘገቡት ተማሪዎች 2 ነጥብ 8 ሚሊየን ብቻ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ በትምህርት ዘመኑ በሁለት ዙር በተደረጉ ኢ-መደበኛ ምዝገባዎች የተመዘገቡት 76 ሺህ ተማሪዎች ብቻ መሆናቸውም ነው የተገለጸው፡፡

መድረኩ በትምህርት ዘርፍ በደረሰው ጉዳት ላይ በመምከር የቀጣይ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በደሳለኝ ቢራራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.