Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮ-ጂቡቲ ምድር ባቡር ላይ በኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ምክንያት ያጋጠመውን የትራንስፖርት መስተጓጎል ለመፍታት እየሠራ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ምክንያት የተከሰተውን የትራንስፖርት መስተጓጎል ለመፍታት ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የኢትዮ-ጂቡቲ ምድር ባቡር አክሲዮን ማኅበር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ታከለ ኡማ (ኢ/ር) ገለጹ።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ባጋሩት መልዕክት፤ ሰሞኑን በኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ምክንያት የተፈጠረውን የአሠራር ችግር ለመፍታት ርብርብ እየተደረገ ነው፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጡም ላለፉት አራት ተከታታይ ቀናት በተቋማቸው ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

የተፈጠረውን መስተጓጎል ለማካካስም፤  በቀጣይ ቀናት፣ የጅምላ ጭነት እና የኮንቴይነር ጭነት አገልግሎት ለማመቻቸት እየተሠራ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

በተለይም እያንዳንዱን ፉርጎ እና ኮንቴይነር በተናጠል ከመቁጠር ይልቅ፤ የባቡር ጉዞ ቁጥሩን በመጠቀም በጅቡቲ ጉምሩክ ያለውን የሠነድ አሰጣጥ ሂደት ቀላል እያደረግን ነው ብለዋል።

እየተሠሩ የሚገኙ ማስተካከያዎች፤ ሥራዎችን ለማፋጠን እና መዘግየቶችን ለመቀነስ ያለመ መሆኑን አስገንዝበው፤ ደንበኞች ላሳዩት ትዕግስት አመሥግነዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.