Fana: At a Speed of Life!

የአሜሪካ አደራዳሪዎች ከሩሲያና ዩክሬን ተደራዳሪዎች ጋር በተናጠል ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሩሲያ ዩክሬንን ጦርነት ለማስቆምና ሰላም ለማምጣት የአሜሪካ አደራዳሪዎች ከሩሲያና ዩክሬን ተደራዳሪዎች ጋር በተናጠል ተወያይተዋል።

በሀገራቱ መካከል ሰላም ለማምጣት አሜሪካ የጀመረችው ጥረት የቀጠለ ሲሆን፤ የአሜሪካ አደራዳሪዎች ከሩሲያና ከዩክሬን ተደራዳሪዎች ጋር በተናጠል እንደተወያዩ ቢቢሲ ዘግቧል።

ሳኡዲ አረቢያ የሚገኙት የዩክሬን መከላከያ ሚኒስትር ሩስተም ኡሚሮቭ ከአሜሪካ አደራዳሪዎች ጋር የነበራቸውን ቆይታ ፍሬያማ እንደነበር በኤክስ ገጻቸው አስፍረዋል።

በውይይታቸው ስለ ኃይልና ወሳኝ መሰረተ ልማት ተቋማት ደህንነት ጥበቃን ጨምሮ ፍትሃዊና ዘላቂ ሰላም ማስፈን የተመለከቱ ነጥቦች አንስተናል ብለዋል።

ከሩሲያ በኩል ከፍተኛ ልምድ ያላቸው ዲፕሎማቱ ግሪጎረ ካራሲን የሩሲያ ደህንነት መስሪያ ቤት አማካሪው ሰርጌይ በሲዳ በድርድሩ ተሳታፊ መሆናቸው በመረጃው ተገልጿል።

ድርድሩ ዛሬም እንደሚቀጥል የተገለጸ ሲሆን ዋና ዓላማውም በጥቁር ባህር አካባቢ የተኩስ አቁም ብርሃን የሚፈነጥቅ ሁኔታ ላይ መድረስ መሆኑ ነው የተጠቆመው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሀገራቱ የሩሲያና ዩክሬን ከፍተኛ ባለስልጣናት ተኩስ ለማቆም የሚያስችል ውሳኔ ላይ ለመድረስ ሳኡዲ አረቢያ በሚገኙበት ወቅት የድሮን ጥቃት ሲሰነዝሩ ማደራቸው ተሰምቷል።

ሩሲያ ሌሊቱን በዩክሬን ላይ 99 የድሮን ጥቃት መሰንዘሯን የዩክሬን ባለስልጣናት ሲገልጹ፤ በምላሹ ደግሞ ኪዬቭ በሩሲያ ግዛት ውስጥ መጠነ ሰፊ የድሮን ጥቃት ሰንዝራ አራት ወታደራዊ ሄሊኮፕተሮችን መደምሰሷን አስታውቃለች።

የሩሲያ ወታደራዊ ባለስልጣናት በበኩላቸው ዩክሬን በሩሲያ ላይ ጥቃት መሰንዘሯን ገልጸው፤ ከ28 በላይ የድሮን ጥቃቶችን ማክሸፋቸውን ተናግረዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.