Fana: At a Speed of Life!

ሀገር በቀል የሕክምና ዕውቀቶችን ለማሳደግ በቅንጅት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገር በቀል የሕክምና እውቀቶችን በምርምር ለማሳደግ፣ ለመጠበቅና ለትውልድ ለማሸጋገር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የአርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ገለጸ።

ኢንስቲትዩት በሕክምና ዘርፍ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮና ከክልሉ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንዲሁም ከጂንካ ዩኒቨርሲቲ ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል።

በኢትዮጵያ ሀገር በቀል ዕውቀቶችን ለዘመናዊው ህክምና በግብአትነት ለመጠቀም ትኩረት መሰጠቱን የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አፈወርቅ ካሱ (ፕ/ር) ገልጸዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ ከጤና ሚኒስቴር፣ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከሌሎች የምርምር ተቋማት ጋር በሀገሪቱ የሚገኙ ሀገር በቀል እውቀቶች በምርምር ለማሳደግ፣ ለመጠበቅና ለትውልድ ለማሸጋገር በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በሀገር ውስጥ የሚገኙ የመድሃኒት ፋብሪካዎች በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከውጭ የሚያስገቧቸውን የህክምና ግብአቶች በሀገር ውስጥ እንያገኙ ለማስቻል እየተሰራ መሆኑንም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ኩሴ ጉድሼ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ሀገር በቀል ዕውቀቶችን በጥናትና ምርምር በማሳደግ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ዩኒቨርሲቲው ከምርምር ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ ለሚገኙ ሀገር በቀል የህክምና ዕውቀቶች ዕውቅና ለመስጠት እየተሰራ መሆኑም የተገለጸ ሲሆን፤ የተቋማቱ ስምምነት በዘርፉ የተጀመሩ የምርምር ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ ያግዛል መባሉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.