የብሔራዊ በጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት 12ኛ ዙር ሰልጣኞች ተመረቁ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የብሔራዊ በጎ ፈቃድ ማኅበረሰብ አገልግሎት የ12ኛ ዙር የስልጠና ማጠቃለያ መርሐ ግብር በአዲግራት፣ ዋቸሞ እና ወራቤ ዩኒቨርሲቲዎች ተካሂዷል፡፡
ተመራቂዎቹ በአዲግራት፣ ዋቸሞ እና ወራቤ ዩኒቨርሲቲዎች ስልጠና የወሰዱ ከ3 ሺህ 460 በላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች መሆናቸውን የሰላም ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ላለፉት አምስት ዓመታት የሰላም አምባሳደር በመሆን ሀገራዊ አንድነትና ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር ረገድ ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገቡ እንደሆኑም ተገልጿል፡፡
ወጣቶቹ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት ከስልጠናው ጋር በማስተሳሰር በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ተሰማርተው የማኅበረሰብ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡
መርሐ ግብሩ በዜጎች መካከል ማኅበራዊ ትስስር እንዲጎልብት፣ ሀገራዊ አንድነትና አብሮነት እንዲጠናከር ለማድረግና ሀገራቸውን እንዲያውቁ ሰፊ ዕድል የሚፈጥር ነው ተብሏል፡፡
በተመሳሳይ የሰላም ሚኒስቴር “በጎነት በአብሮነት” በሚል መሪ ሐሳብ በጅማ ዩኒቨርሲቲ 1 ሺህ 256 የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰልጣኞችን በዛሬው ዕለት አስመርቋል፡፡