የሰላም ሚኒስቴር 1 ሺህ 256 የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰልጣኞችን አስመረቀ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሰላም ሚኒስቴር “በጎነት በአብሮነት” በሚል መሪ ሐሳብ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ 1 ሺህ 256 የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰልጣኞችን በዛሬው ዕለት አስመርቋል።
ሚኒስቴሩ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ሲያሰለጥናቸው የቆየውን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰልጣኞችን ነው እያስመረቀ የሚገኘው።
በስነ ሥርዓቱ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ም/ሰብሳቢ ፈቲሂ መሂዲ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት÷ ሀገራዊ እና ቀጣናዊ ሰላምን ለማረጋገጥ ተመራቂዎች የጀመሩትን በጎ ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉና ሀገራዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
የሰላም ሚኒስቴር የብሔራዊ በጎ ፈቃድ አገልግሎት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ገመቺሳ ኢትቻ በበኩላቸው÷ እስካሁን በመላው ሀገሪቱ 80 ሺህ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሰልጠናቸውን ገልጸዋል።
በዛሬው ዕለትም በአራት ዩኒቨርሲቲዎች ከ4 ሺህ በላይ ወጣቶች መመረቃቸውን ተናግረው፤ በቀጣይ በክረምት 30 ሺህ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለማሰልጠን መታቀዱን አንስተዋል።
በበሪሳ ኃይለማርያም