የኢትዮጵያን ብልጽግና ዕውን ለማድረግ ያሉንን ሃብቶች በሚገባ መጠቀምና ማልማት ይገባል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያን ብልጽግና ዕውን ለማድረግ ያሉንን ሃብቶች በሚገባ መጠቀምና ማልማት ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በአፋር ክልል የግብርና እና የኢንዱስትሪ አቅሞችን የሚያሳዩ ቁልፍ የልማት ፕሮጀክቶችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡
በዚህ ወቅትም በክልሉ በእንሳሰት መኖ፣ ስንዴ፣ ኢንዱስትሪ እና በኮሪደር ልማት እየተከናወኑ ያሉ ሰፋፊ የመሰረተ ልማት ግንባታ ሥራዎች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ለአብነትም ለእንስሳት መኖ በ500 ሄክታር ገደማ በመስኖ እርሻ የታረሰውን አዲሱ የሳር ዝርያ አንስተው÷በድርቅ ምክንያት ከብቶች እንዳይጎዱ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ልምምድ መሆኑንና የተጀመሩ ሥራዎች ማስፋት እንደሚገባ አመልክተዋል።
ከ1 ሺህ 500 ሄክታር በላይ መሬት ላይ በበጋ መስኖ ስንዴ እየተመረተ እንደሚገኝ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በአፋር ክልል ባለው ሙቀት ከዚህ ቀደም ስንዴ ማምረት የማይታሰብ ነበር ብለዋል።
በቀን 300 ሺህ ዳቦ እና 450 ኩንታል ዱቄት የማምረት አቅም ያለው በሰመራ ከተማ በቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት ተገንብቶ የተመረቀው የዳቦ ፋብሪካ የከተማዋን ነዋሪ ፍላጎት ማሟላት እንደሚያስችል አንስተዋል፡፡
በክልሉ ያለው የኮሪደር ልማት ሥራ በመልካም ጅማሮ ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው÷የአረንጓዴ ልማት ሥራና የከተማን ደረጃ ለመጠበቅ የሚከናወነው ተግባር እስከ ቀጣዩ ዓመት መጀመሪያ ባለው ጊዜ ሊጠናቀቅ እንደሚችል አብራርተዋል።
በክልሉ የእርሻ እና ኢንዱስትሪ ሥራው አመርቂ መሆኑን ጠቁመው÷ይሁንና ክልሉ ካለው ሃብት እና ፀጋ አንጻር ገና ብዙ መስራት እንደሚጠበቅ፤በዚህም ለኢትዮጵያ ዕድገትና ብልጽግና የሚጠቅም ትልቅ አቅም እንዳለው ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ እና የተያዘውን ግብ ለማሳካት በሀገሪቷ ያሉትን ሃብቶች አይንን ገልጦ በመመልከት እንዲሁም በትጋት በመስራት መጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል።
የሚታሰበውን ብልጽግና ለማምጣት ጅማሮው ጥሩ ቢሆንም መፍጠን እና መፍጠር አለብን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ይህ ሲሆን የተሟላ የልማት ገጽታ መላበስ እንችላለን ብለዋል።
በዮናስ ጌትነት