የወልዲያ-ሮቢት መንገድ የሀሚድ ወንዝ የብረት ድልድይ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የወልዲያ – ሮቢት መንገድ የሀሚድ ወንዝ የብረት ድልድይ ጥገና ተጠናቅቆ ለትራፊክ አገልግሎት ክፍት መደረጉን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታውቋል።
ድልድዩን በኮንክሪት ለመገንባት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ሲሆን÷ሥራው በተያዘው ዓመት መጨረሻ እንደሚጀመር ተመላክቷል፡፡
45 ነጥብ 7 ሜትር ርዝመት ያለው የሀሚድ ወንዝ የብረት ድልድይ ከዚህ ቀደም ከተፈቀደው ክብደት በላይ በጫነ ከባድ ተሽከርካሪ ጉዳት ደርሶበት እንደነበር ይታወቃል።
በወቅቱ ተለዋጭ መንገድ በማዘጋጀት ተሽከርካሪዎች እንዲገለገሉ ማድረግ መቻሉን የአስተዳደሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
አሁን ላይም በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የኮምቦልቻ መንገድ ጥገና ዲስትሪክት እና የድልድይና ስትራክቸር ዳይሬክቶሬት ባደረጉት ጥገና ለትራንስፖርት እንቅስቃሴ ክፍት መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
አሽከርካሪዎች በሕግ በተፈቀደው የጭነት ልክ በመጫን እንዲገለገሉም አስተዳደሩ አሳስቧል።