ላለፉት 3 ቀናት የተቋረጠውን የኢትዮ- ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ለማስጀመር እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከመኢሶ እስከ ጅቡቲ ባጋጠመ የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ ላለፉት ሶስት ቀናት የተቋረጠውን የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ለማስጀመር እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታውቋል።
የኢትዮ- ጅቡቲ ባቡር አክሲዮን ማህበር ቺፍ ኦፕሬሽን ኦፊሰር አያና በርኬሳ ለፋና ዲጂታል እንደገለጹት÷ከረቡዕ ሌሊት 6 ሰዓት ጀምሮ በኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ ምክንያት የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ተስተጓጉሏል።
የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ታወሮች ላይ ባጋጠመ ችግር ከመኢሶ እስከ ጅቡቲ ያለው የባቡር መስመር ኤሌክትሪክ እያገኘ ባለመሆኑ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቱ መቋረጡን አስረድተዋል፡፡
በዚህም 18 ባቡሮች መንገድ ላይ ለመቆም መገደዳቸውን ገልጸው÷ወደብ ላይም የጭነት ሥራው መስተጓጎሉን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ስድስት የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ባቡሮች መቆማቸውን ነው የገለጹት።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን በበኩላቸው÷አዋሽ አካባቢ ሶስት የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ታወሮች ስርቆት ተፈጽሞባቸው መውደቃቸውን ለፋና ዲጂታል አረጋግጠዋል
የተፈጠረውን ችግር ተከትሎም ከአዋሽ ጀምሮ ወደ ምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጡን ተናግረዋል።
ችግሩን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው÷ ይህም የተወሰኑ ቀናት ሊወስድ እንደሚችል አመልክተዋል።
አንድ ቦታ ላይ በኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ታወሮች ላይ የሚፈጸመው ስርቆት ሌሎች አካባቢዎችን የሚጎዳ መሆኑ ጉዳዩን አሳሳቢ እና አስቸጋሪ አድርጎታል ነው ያሉት፡፡
ስለሆነም የሚመለከታቸው አካላት እና ሕብረተሰቡ ትኩረት በመስጠት ለኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ታወሮች ጥበቃ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
በብርሃኑ አበራ