50 በመቶ የሚሆነውን የኢትዮጵያን የወጪ ገቢ ጭነት በባቡር ለማጓጓዝ እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) 50 በመቶ የሚሆነውን የኢትዮጵያን የወጪ ገቢ ጭነት በባቡር ለማጓጓዝ እየተሰራ እንደሚገኝ የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር አክሲዮን ማህበር የማጓጓዝ አቅሙን በየዓመቱ በ14 ነጥብ 2 በመቶ እያሳደገ መምጣቱንም ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡
አብነትም ወደ ውጭ ከተላከው ቡና 98 በመቶ የሚሆነው በባቡር የተጓጓዘ ሲሆን ማዳበሪያን ጨምሮ የመልቲ ሞዳልና ዩኒ ሞዳል ኮንቴነር ጭነቶችን፣ የቁም እንስሳትን፣ ከባድ ማሽኖችን፣ አውቶቡሶችና አዳዲስ የጭነት ተሽከርካሪዎች በባቡር ተጓጉዘዋል፡፡
የሚበላሹ ጭነቶችን በኮንቴነር አሽጎ በማጓጓዝ ጥራታቸውን እንደጠበቁ ለውጪ ገበያ በማቅረብ ከውጭ ንግዱ ሊገኝ የሚታሰበውን ገቢ በማስጠበቅ በኩል የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ሚናውን እየተወጣም እንደሚገኝ ተመላክቷል፡፡
አሁን ላይም የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር የኢትዮጵያን 50 በመቶ የወጪ እና ገቢ ጭነት ለመሸፈን፣ በየቀኑ 14 ባቡሮችን በማሰማራት አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም የጭነት ባቡር ጉዞ ፍጥነትን በሰዓት ወደ 58 ኪሎ ሜትር ለማድረስ እንዲሁም በባቡር የሚሰጠውን አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ዲጂታል ለማድረግ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል መባሉን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡