በተግባር ውጤት በማስመዝገብ አርአያ የሚሆን አመራር ለማፍራት እየተሰራ ነው – አቶ ፍቃዱ ተሰማ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በተግባር ውጤት የሚያስመዘግብና አርአያ የሚሆን አመራር ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና በሚኒስትር ማዕረግ የፓርቲው ዋና ጽ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ ገለጹ፡፡
አቶ ፍቃዱ ፓርቲው ከሰሞኑ ያካሄዳቸውን የውይይት መድረኮችና የፓርቲው ቀጣይ ሥራዎች አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ ÷ ብልጽግና ፓርቲ ከ15 ነጥብ 7 ሚሊየን በላይ አባላት እና ከ104 ሺህ በላይ አመራሮች እንዳሉት ገልጸዋል፡፡
በአመራሮች እና በፓርቲ አባላት መካከል የተግባር እና የዓላማ አንድነት ለማምጣት በርካታ ሥልጠናዎች መሰጠታቸውንና የምዘና ሥርዓት ተዘርግቶ ግምገማ ሲደረግ መቆየቱን አንስተዋል፡፡
በፓርቲው አመራሮችና አባላት መካከል የዓላማ አንድነት ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ገልጸው÷ ለዚህም ፓርቲው አመራሮችንና አባላቱን የማጥራት ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
በሁለንተናዊ ብልጽግና ሃሳብና በተግባራዊ ውጤት ክፍተት ያለባቸውን አመራሮችና አባላት የማረም እንዲሁም በብልሹ አሰራር ውስጥ የሚገኙ አመራሮችና አባላትን የማጥራትና የማረም ሥራ እንደሚከናወን አመልክተዋል፡፡
በተጨማሪም የአዳዲስ አባላት ምርመራ በሚደረግበት ወቅት ከብዛት ይልቅ ጥራት ላይ በማተኮር የብልጽግናን ሀሳብ የሚቀበል እና በተጨባጭም ለውጥ ያመጣሉ ተብሎ በሚታመንባቸው አባላት ላይ ትኩረት ይደረጋል ነው ያሉት፡፡
አዳዲስ አባላት በሥነ-ምግብራቸው ሞዴል የሆኑ እንዲሁም ችግሮች ሲመጡ የሚጋፈጡ እንጂ በችግሮች ሸብረክ የማይሉ መሆን እንዳለባቸው ነው ያስገነዘቡት፡፡
ፓርቲው ምሁራን፣ ወጣቶችና ሴቶችን ያሳተፈ አዳዲስ አመራሮችን ለማፍራትና መዋቅራዊ አደረጃጀቶችን ለማጠናከር ድጋፍ እና ክትትል የማድረግ ሥራ እንደሚያከናውን ጠቅሰዋል፡፡
የፓርቲው አመራር እና አባላት ከመንግስት ተግባራዊ በሚደረጉ የተለያዩ ኢኒሼቲቮች ላይ በመሳተፍ ሁለንተናዊ ብልጽግናን እውን ለማድረግ ሊሰሩ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
በሚኪያስ አየለ