ኢትዮጵያ ለኬንያ በቀን 265 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እያቀረበች ነው
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እና ኬንያ በተፈራረሙት የኃይል ሽያጭ ስምምነት መሰረት ለኬንያ በቀን 265 ሜጋ ዋት ኃይል እየቀረበ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኢትዮ-ኬኒያ ባለ 500 ኪሎ ቮልት ኮንቨርተር ጣቢያ ምስራቅ አፍሪካን በኃይል ለማስተሳሰር ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑ ተገልጿል።
በጣቢያው የጥገናና የኦፕሬሽን ባለሙያ አቶ መኮንን ካሴ እንደተናገሩት ጣቢያው ከወላይታ ሶዶ ቁጥር ሁለት የማከፋፈያ ጣቢያ በአራት ባለ 400 ኪሎ ቮልት ገቢ መስመሮች ተቀብሎ፣ 12 ኮንቨርተር ትራንስፎርመሮችን እና 1ሺህ 680 ታሪስተሮች(thyristors) ተጠቅሞ ኃይል የሚያስተላልፍ ነው።
ጣቢያው 2000 ሜጋ ዋት ኃይል የመሸከም አቅም ባላቸው በሁለት ፖሎች እና ከኢትዮጵያ እስከ ኬንያ በተዘረጋ 1ሺህ 60 ኪሎ ሜትር የማስተላለፊያ መስመር አማካኝነት ኃይል እያስተላለፈ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ከኬንያ ጋር ባለው የኃይል ሽያጭ ስምምነት መሰረት በአሁኑ ወቅት በቀን 18 ሰዓት ማለትም እስከ ምሽት 6 ሰዓት 200 ሜጋ ዋት እንዲሁም ከዚያ በኋላ በሚኖረው ቀሪ 6 ሰዓት ደግሞ 65 ሜጋ ዋት ኃይል እየቀረበ ይገኛል ብለዋል።
ጣቢያው በስምምነቱ መሠረት እየጨመረ የሚሄደውን የኃይል አቅርቦት እና ወደ ታንዛኒያ ኃይል ለማስተላለፍ የተያዘውን ዕቅድ ማሳካት የሚያስችል አቅም እንዳለውም ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ ከሌሎች ሀገራት ጋር የሚደረጉ የኃይል ሽያጭ ስምምነቶችን ተከትሎ አስተማማኝና ኃይል በማስተላለፍ ለአህጉራዊ የኃይል ትስስር መሳለጥ የሚያደርገውን አስተዋጽኦ ለማስቀጠል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ጣቢያው የኃይል ኤክስፖርቱን ለማሳደግ የተያዘውን ጥረት ለመደገፍ አቅም ማጎልበትን ጨምር የተለያዩ የማሻሻያ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ መግለጻቸውን የተቋሙ መረጃ ያመላክታል።