ዘመቻ አንድነት በሚል በአማራ ክልል ትንኮሳ ለመፈፀም የሞከረው ራሱን ፋኖ ብሎ የሚጠራው ቡድን ላይ እርምጃ ተወሰደ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በብርጋዲየር ጄኔራል ምግበይ ኃይለና ግብረ አበሮቹ አደራጅነትና አይዞህ ባይነት ዘመቻ አንድነት በሚል ስያሜ በተለያዩ የአማራ ክልል ወረዳዎች ትንኮሳ ለመፈፀም የሞከረው ፅንፈኛው ቡድን ላይ እርምጃ መውሰዱን መከላከያ ሠራዊት አስታወቀ፡፡
ብርጋዲየር ጄኔራል ምግበይ ዕድሜ ልኩን በታሪኩ ግጭት እየጠመቀ የትግራይን ሕዝብ ወደ ጦርነት በማስገባት ያለ ምንም ወታደራዊ ዕውቀት ወጣቱን ወደ እሳት አሥገብቶ የማስፈጀት ታሪክ ያለው ፀረ ሠላምና ፀረ ልማት አራማጅ ነው ብሏል መከላከያ ሠራዊት በማኅበራዊ ትሥሥር ገጹ ባጋራው መረጃ።
ውጊያ ከብዶት የሸሸውን ወጣት ለምን ሸሸህ በሚል ሰበብ በጅምላ የመረሸን ልምድ ያለው እና ያለ ዕውቀት የትግራይን ወጣቶች ደም ሲመጥ የቆየ መሆኑ ሳያንሰው፤ አሁን ላይም የፅንፈኛው መሪዎች ነን ባዮች አማካኝነት የሠላም ፈላጊውን የአማራን ወጣት ሕይዎት ለመቅጠፍ እንቅስቃሴ የጀመረ መሆኑ ታውቋል ብሏል መረጃው።
ባለፈው ጊዜ በነበረው የሰሜኑ ጦርነት በመቶ ሺህ የሚቆጠር የትግራይ ወጣትን እየረሸነ እያሥረሸነ የፈጀ የጥቁር ታሪክ ፀሃፊነቱ ሳያንስ፤ አሁን ላይም መሠል ድርጊት ለመፈፀም እየተንቀሳቀሰ ነው ተብሏል፡፡
ምዕራብ ትግራይን አስመልሳለሁ በሚል እሳቤ ሁለት ጊዜ የፌዴራል መንግስት ሠራዊትን ለማጥቃት ሞክሮ፤ በ10 ሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶችን ያስበላ ውጊያ እምቢ ሲለው የራሱን ታጣቂዎች ረሽኖና ገድሎ ውጊያው ሳይሳካለት አከርካሪው ተመትቶ ሸሽቷል ብሏል መከላከያ ሠራዊት።
ምግበይ ኃይለ ዘረፋና ሌብነት የተካነበት መደበኛ ሥራው ነው ያለው የመከላከያ ሠራዊት መረጃ፤ በአሁኑ ጊዜ የትግራይን ወርቅ እየዘረፈ በኤርትራ በኩል አድርጎ እየሸጠ ይገኛል ሲል ገልጿል፡፡
በኢህአዴግ ዘመን በዘረፋና ሌብነት ታዋቂ የነበረ ብቻ ሳይሆን፤ በሰረቀውና በዘረፈው ገንዘብ አዲስ አበባ ላይ ፎቆችን የደረደረ አለፍ ሲልም ዱባይ ላይ ፎቆችን ለመሥራት በቅርብ ጊዜ የተዋዋለ ሥለመሆኑ በሶሻል ሚዲያ ሲነገር ቆይቷል ነው የተባለው።
በጦርነት ከቀቀለው ወጣት በተጨማሪ የረሸናቸው በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች በመኖራቸው፤ ትግራይ ሰላም እንድትሆን ከቶውንም አይፈቅድም ሲል ገልጿል መከላከያ ሠራዊት፡፡
ምክንያቱም ደግሞ የትግራይ ሕዝብ ልጆቹን ይጠይቀኛል የሚል ስጋት አንደኛው ሲሆን ሌላኛው ደግሞ እያደረገ ያለው የወርቅ ዘረፋ እንዳይጋለጥበት በማሠብ ነው ነው የተባለው፡፡
በሌላ በኩል ምግበይ ኃይለ የፕሪቶሪያን ስምምነት እንዲፈርስ እንዳይሳካ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ያለ ከመሆኑም በላይ፤ የጊዜያዊ መሥተዳድሩን ማህተም ለመንጠቅ እና በኃይል አፍርሶ ሥልጣን ለመያዝ የሞከረ የፀረ ሠላምና ፀረ ልማት አራማጅ ነው ብሏል መረጃው።
የሠላም ጠንቅ የሆነው ምግበይ ኃይለ ለዚህ መሰሪ ተግባሩ ጽንፈኛው ኃይል እንደ ተባባሪነት በመጠቀም በራሱ ክልል ላይ ያልተገባ ውድመት እንዲፈፅም አዝዞታል ነው ያለው። ነገር ግን ዘመቻ አንድነት በሚል ስያሜ ፅንፈኛውን አሥተባብሮ በጀመረው ትንኮሳ ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ ደርሷበታል ይላል የመከላከያ ሠራዊት መረጃ።
በደቡብ ጎንደር፣ በምዕራብ ጎንደር፣ በሰሜን ጎጃም፣ በምስራቅ ጎጃም፣ በምዕራብ ጎጃም እንዲሁም በሰሜን ወሎ የምግበይ ኃይለ ተላላኪ ፅንፈኞች በለኮሱት እሳት ተለብልበዋል ተብሏል፡፡
በዚህ ሁለት ቀናት ብቻም 317 የተገደለ፣ 41 የተማረከ፣ 125 የቆሰለ፣ 27 እጅ የሠጠ፣ 51 በምህረት የገባ፣ 15 መረጃ አቀባይ የተያዘ፣ በድምሩ 576 የሠው ኪሳራ ደርሶበታል ይላል መረጃው፡፡
እንዲሁም 1 መትረየስ፣ 119 ክላሽ፣ 46 ኋላቀር መሣሪያ፣ 8 ሽጉጥ፣ 22 ቦምብ፣ 2 ሺህ 290 የተለያዩ ዓይነት ተተኳሾች፣ 28 ትጥቅ፣ የመገናኛ ራዲዮ፣ ተሽከርካሪ፣ ባጃጅ፣ ሞተር ሳይክል እና ሌሎች ቁሶችም በሠራዊታችን ቁጥጥር ስር ውለዋል ይላል መረጃው።
ይህ በምግበይ ኃይለ እና በግብረ አበሮቹ አይዞህ ባይነት የተጋለበው ፅንፈኛ ቡድን፤ በዚህ ልክ ኪሳራ የደረሰበት ሲሆን በሕይዎት የተረፈው የትም የተበታተነ መሆኑ ተረጋግጧል ተብሏል፡፡