Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ የደንብ ልብስ መለያን አስመስለው በመልበስ ሕዝቡን ሲያሳስቱ ነበር የተባሉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን የቀድሞ ዩኒፎርምን አስመስለው በመልበስ ሕዝቡን ሲያሳስቱ ነበር የተባሉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ሸጋው ጫኔ አንለይ፣ መሃመድ ሀምዛ ያሲን፣ አቤኔዘር ተስፋዬ በየነ እና ጌትነት ደምለው ዳምጤ የተባሉ ግለሰቦች ናቸው፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ተጠርጣሪዎቹ ዩኒፎርሙን አስመስለው በመልበስ የባለስልጣኑ ሰራተኞች አላስፈላጊ ተግባራትን እንደፈጸሙ በማስመሰል የሱቅ ማስታወቂያ ሰርተዋል፡፡

በዚህም በጎዳና ንግድ ላይ የሚተዳደሩ ግለሰቦችን ንብረት በመበተንና በመደብደብ የባለስልጣኑን ገጽታ በሚያንቋሽሽ መልኩ ሀሰተኛ ቪዲዮ አዘጋጀተው በቲክቶክ ማሰራጨታቸውን ነው ያስረዱት፡፡

በተቋሙና በሰራተኞቹ ላይ እንዲሁም በሕዝብ ዘንድ አሉታዊ ስሜት እንዲፈጠር አስበው የተቋሙን የቀድሞ የደምብ ልብስ የሚመስል አዘጋጅተው ድርጊቱን መፈጸማቸውም ተጠቅሷል፡፡

ግለሰቦቹ በዚህ ሕገ ወጥ ተግባራቸውም በርካታ ሰዎችን እንዳሳሳቱ ነው የገለጹት፡፡

ተጠርጣሪዎቹ አሁን ላይ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየተጣራ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡

ዜጎች አላስፈላጊ ጥቅም ለማግኘት ሲባል መሰል ተግባራትን ከመፈጸም እንዲቆጠቡም ኮማንደሩ አሳስበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.