ዋልያዎቹ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከግብፅ ጋር ጨዋታቸውን ያደርጋሉ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የ2026 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ አምስተኛ ጨዋታውን ከግብፅ ብሔራዊ ቡድን ጋር ያከናውናል።
ዋልያዎቹ በምድቡ ካደረጓቸው አራት ጨዋታዎች ሶስት ነጥብ በመያዝ በምድቡ አምስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ፤ ተጋጣሚያቸው የግብፅ ብሔራዊ ቡድን በ10 ነጥብ ምድቡን በበላይነት እየመራ ይገኛል።
ካዛብላንካ በሚገኘው ላርቢ ዛውሊ ስታዲየም ሌሊት 6 ሠዓት ላይ የሚደረገውን የሁለቱን ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ ሞሪሸሳዊው ዳኛ ፓትሪስ ሚላዛር በመሐል ዳኝነት ይመሩታል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በጨዋታው አረንጓዴ ማልያ፣ ቢጫ ቁምጣ እና ቀይ ካሶተኒ ሲለብስ፤ ተጋጣሚው የግብፅ ብሔራዊ ቡድን ቀይ ማልያ ነጭ ቁምጣ እና ጥቁር ካሶተኒ ለብሶ ወደ ሜዳ እንደሚገባ የፌዴሬሽኑ መረጃ ያመላክታል።
በዚሁ ምድብ የሚገኙት ቡርኪናፋሶ እና ጅቡቲ የምድብ አምስተኛ ጨዋታቸውን ዛሬ ምሽት 1 ሠዓት ላይ ያደርጋሉ።
በኢትዮጵያ ምድብ የሚገኙት ሴራሊዮን እና ጊኒ ቢሳው ትናንት ምሽት ያደረጉት ጨዋታ፤ በሴራሊዮን 3 ለ 1 አሸናፊነት ተጠናቅቋል።
ሴራሊዮን ማሸነፏን ተከትሎ ነጥቧን ስምንት በማድረስ በምድቡ ሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችላለች።
በወንድማገኝ ፀጋዬ